ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሆስፒታሎችን የአሰራር ማነቆዎች ለመፍታት እያደረገችው ያለው ማሻሻያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል አምጥቷል- የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ የሆስፒታሎችን የአሰራር ማነቆዎች ለመፍታት እያደረገችው ያለው ማሻሻያ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል እንዲመጣ ማድረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ሲካሄድ የቆየው 47ኛው የዓለም ሆስፒታል ኮንግረስ ተጠናቋል።

"የወደፊት ሆስፒታሎች" በሚል መሪ ሀሳብ በተከናወነው ኮንግረስ ከ65 ሀገራት የተውጣጡ ከ1500 በላይ ልዑካን ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለው የሆስፒታሎች የስርዓት ማነቆዎችን መሰረት ያደረገ ሪፎርም (SBFR) ምርጥ 15 ፈጠራ የታከለባቸው የጤና አገልግሎቶች ማሻሻያ ስራዎች መካከል አንዱ ሆኖ በኮንግረሱ ላይ በተሞክሮነት ቀርቧል።

ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው ሪፎርም የተወሰነ መሰረተ ልማትና የሰው ኃይል በመጠቀም የሆስፒታሎችን የአገልግሎት አሰጣጥና ክብካቤ ማሻሻልን ትኩረቱን ያደረገ ነው።

በማሻሻያው ላይ ማብራሪያ የሰጡት የጤና ሚኒስቴር የጤና ስርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አባስ ሀሰን ሪፎርሙ የሆስፒታሎችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ጥራትን በማሻሻል አመርቂ ውጤቶችን ማስገኘቱን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ መንግስት መር የጤና ኢኖቬሽን ስርዓት መዘርጋቱንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በጤና ስርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ያለሙ አዳዲስ አሰራሮችን ለመፍጠርና በትግበራ ላይ ያሉትን ስራዎች ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

ኮንግረሱ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የጤና ክብካቤን ለማበልጸግ አገር በቀል መፍትሔዎችና ፈጠራ የታከለባቸው አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር የሚያስችል ምቹ እድል አጋጣሚ እንደሚፈጥር ነው ዶክተር አባስ የገለጹት።

በኮንግረሱ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶች ላይ በመሳተፍ የልምምድ ልውውጥ አድርጓል።

ኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ያላትን ልምድና አዳዲስ አሰራሮች በመዘርጋት ያላትን ተሞክሮ ለኢትዮጵያ በተዘጋጀው የኢኖቬሽን ማሳያ ቦታ (Innovation Show Booth) ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ ልዑካን በማካፈል ውጤታማ ተግባር መከናወኑ ተገልጿል።

ኮንግረሱ የአጋርነትና የትብብር እድሎችን በማጠናከር የኢትዮጵያ የጤና ስርዓት ላይ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም