ቀጥታ፡

ስዩም ከበደ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017 (ኢዜአ):- ስዩም ከበደ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ።

አሰልጣኝ ስዩም ለማጣሪያው ጨዋታ ዝግጅት ለ38 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።

እ.አ.አ በ2025 በሚካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ይካሄዳል።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የማጣሪያ ድልድል ባለፈው ሳምንት በዳሬ ሰላም ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

ስዬም ከበደ በማጣሪያ ውድድሩ ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው ዛሬ መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ዐቢይ ካሣሁንና አምሳሉ እስመለዓለም ረዳት አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን ገልጿል።

በተያያዘም አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ብሔራዊ ቡድኑ ለማጣሪያ ውድድሩ ለሚያደርገው ዝግጅት ለ38 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ዙር ጥሪ አድርገዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከነገ ጀምሮ በመሰባሰብ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።

24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ በስድስት ዞኖች ተከፍሎ እንደሚካሄድና 48 ሀገራት እንደሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም