ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአደጋ ስጋት ቀነሳ ስትራቴጂዎች ወቅታዊ ለውጦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል - አምባሳደር ፀጋአብ ከበበው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017 (ኢዜአ):- በዓለም አቀፍ ደረጃ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂዎች ከጊዜው ጋር የሚሄድ ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሊቀ መንበርነት የመራችው የተባበሩት መንግስታት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጽህፈት ቤት ድጋፍ ቡድን ስብስባ ዛሬ በጄኔቫ ተካሄዷል።

አደጋዎችን የመከላከል አቅምን ማሳደግ ላይ ባተኮረው ስብስባ የጽህፈት ቤቱ አመራሮችን ና አባል አገራት ተሳትፈዋል።

በጄኔቫና ኦስትሪያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው እንደ ዓለም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስትራቴጂዎች ከወቅታዊ ክስተቶችና ፈተናዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

አምባሳደር ፀጋአብ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የአደጋ ስጋት ቅነሳ ጽህፈት ቤት ድጋፍ ቡድን ሊቀ መንበርነቷ ሶስት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮችን ዘርዝረዋል።

አዲስና የቆዩ የአደጋ ስጋቶችን መቀነስን አላማ ያደረገው የሴንዳይ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ማዕቀፍ (ከእ.አ.አ 2015 -2030 የሚቆይ) ትግበራን ማፋጠን ላይ በትኩረት እንደምትሰራ ገልጸዋል።

የቅድመ አደጋ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን ተደራሽነት እንዲሰፋ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቅደመ ማስጠንቀቂያ ለሁሉም ኢኒሺዬቲቭ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጎለብት የማስተባበር ሚና ትወጣለች ብለዋል።

የታችኛው የመንግስት አስተዳደር መዋቅር በአደጋ ስጋት ቅነሳ የእቅድ ቀረጻ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠናክርና የአካባቢ ማህበረሰቦችን አቅም መገንባት እንደሚገባም ነው አምባሳደር ፀጋአብ የገለጹት።

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ልዩ ተወካይ ከማል ኪሾር ተመድ አገራት በአደጋ ስጋት ቅነሳ ላይ እያከናወኗቸው ያሉ ስራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።

እ.አ.አ በ2025 በስዊዘርላንድ በሚካሄደው ስምንተኛው ዓለም አቀፍ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስብስባ፣ የ2024 ማብቂያ ድረስ የሚደረጉ ቀጣናዊ የአደጋ ስጋት ቅነሳ ስብስባዎች፣ በቀጣይ ወር የሚከበረው የዓለም የአደጋ ስጋት ቅነሳ ቀንና የዓለም የሱናሚ አደጋ ግንዛቤ መፍጠሪያ ቀን የተመለከቱ ጽሁፎች ቀርበዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት በግንዛቤ መፍጠሪያ ኢኒሺዬቲቮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።
በውይይቱ ላይ አገራት ለአደጋ ስጋት ቅነሳ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየጨመሩ ለመጡ የከባቢ አየር ፈተናዎች በአንክሮ አስቀድሞ መመልከትና መዘጋጀት እንዳለበት መነሳቱን ኢዜአ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም