በአፍሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተጠረጠሩ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ተለዩ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017(ኢዜአ)፡-  የዓለም ጤና ድርጅት ከዘንድሮው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተጠረጠሩ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች በሽታ መለየታቸውን አስታወቀ።

የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲሲ) በበኩሉ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ  ምላሽ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ የስፑትኒክ ዘገባ አመለክቷል።

ከጥር 1 እስከ መስከረም 8/ 2024 ድረስ ከ720 በላይ በበሽታው ምክንያት ሞት መመዝገቡን ተገልጿል።

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት እስከ መስከረም 8/2024 በአፍሪካ ከበሽታው ጋር የተያያዙ 5ሺህ 789 የበሽታ ምልክቶች በቤተ ሙከራ ሲረጋገጥ 32 ሰዎች መሞታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

በሽታው  በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ  ከተጠረጠሩ 21 ሺህ 835 ጉዳዮች  717 ሰዎች መሞታቸውን በዘገባው ተጠቅሷል።

የዓለም ጤና ድርጅት  የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ  በአገሪቱ  ምሥራቃዊ  ክፍልና በአጎራባች አገሮች የሚያደርሰውን ጉዳት ከፍ አድርጎ መገምገሙን አመላክቷል።

ድርጅቱ የወረርሽኙ ጉዳት በናይጄሪያና በሌሎች የምዕራብ፣ የመካከለኛው እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መጠነኛ  እንደሆነ መታሰቡንና  በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ስላለው ሁኔታ ተመሳሳይ ግምገማ መስጠቱንም  በዘገባው ተገልጿል።

እንደ ስፑትኒክ ዘገባ በአጠቃላይ ከጥር 1/2022 እስከ ሐምሌ 31/2024 በዓለም ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ 103ሺህ  48 የተረጋገጡ ጉዳዮች፤ 229 ሞትን ጨምሮ በ121 አገራት ተመዝግበዋል። 

የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) በበኩሉ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ  ምላሽ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ  ገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዣን ካሴያን ገንዘቡ ከአፍሪካ ህብረት ሀገራት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ከግሉ ዘርፍ ለማሰባሰብ እንደታቀደ አመልክተዋል። 

እንደ ጋቪ እና ዘ ፓንዴሚክ ፈንድ ካሉ ድርጅቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንና ፤ የቴክኖሎጂ ዝውውሮች የክትባት ወጪዎችን 90በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል። 

በተጨማሪም የምዕራቡ ዓለም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ትምህርት መውሰዱንና በዝንጀሮ ፈንጣጣ  ወረርሽኝም  አፍሪካን እንዳልተዉ ማሳየት እንደሚጠበቅበት ማስገንዘባቸውን  አንስቷል። 

ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ወር በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ  ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑን ካወጀ በኋላ የመጣ መሆኑን በዘገበው ተጠቅሷል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም