በአማራ ክልል የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ንግድና ቢዝነስ ስራ እንዲገቡ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የስራ ፈጠራ ውድድር አሸናፊ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ንግድና ቢዝነስ ስራ እንዲገቡ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ ነው
ባህር ዳር ፤ መስከረም 6/2017 (ኢዜአ)፡- በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የስራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ከአማራን ክልል አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች ወደ ቋሚ ንግድና ቢዝነስ ስራ እንዲገቡ የማመቻቸት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ ወጣቶቹ ያሸነፉት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደ የስራ ፈጠራ ሀሳብ ውድድር ነው።
እንዲወዳደሩ ከክልሉ ከተላኩት 63 የፈጠራ ሃሳብ ካላቸው ወጣቶች መካከልም 39ኙ በላቀ ብቃት አሸንፈው የገንዘብ ተሸላሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሻሻል፣ የአገልግሎት ዘርፉን ለማዘመንና መሰል ቴክኖሎጂዎችን መፍጠር የቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
እነዚህ ወጣቶች ያፈለቋቸውን የስራ ፈጠራ ሃሳቦች ወደ ቢዝነስ ቀይረው እንዲሰሩ ቢሮው የመስሪያ ቦታና ብድር እንዲመቻችላቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ቀጣይ ሌሎች የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶችን ከማነሳሳት ባለፈ የፈጠራ ስራዎቹ ተመርተው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚያግዝ እንደሆነ አመልክተዋል።
በዘንድሮው የበጀት ዓመትም 31 ወጣቶችን በአገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የብሩህ ሀሳብ የወጣቶች የስራ ፈጠራ ውድድር ለማሳተፍ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጓዳኝም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሰለጠኑ ወጣቶችን የሙያ ብቃት ምዘና በመስጠት በተለያዩ የውጭ አገራት የስራ ስምሪት ዕድል እንዲያገኙም እንዲሁ።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ በሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች የሙያ ስልጠና ከወሰዱ ወጣቶች መካከል ከ82 ሺህ በላይ ወጣቶች የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ዕድል እንዲያገኙ መደረጉን አስታውሰዋል።
ከዚህም ሌላ በአገር አቀፍ ደረጃ የግብርና ናሙና መረጃን ለማሰባሰብ የተያዘው ግብ እንዲሳካ ለማገዝ በክልሉ ስራ የሌላቸው ከ6ሺህ 100 የሚበልጡ ወጣቶች በዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ስልጠናውን እየወሰዱ ያሉት ወጣቶች የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው እንደሆኑም አመልክተዋል።
ወጣቶቹ የክልሉን የግብርና ናሙና መረጃን በአግባቡ በማሰባሰብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ታስቦ እንደሆነም አቶ ዘመነ አስረድተዋል።
መረጃ ሰብሳቢዎች የናሙና ቆጠራውን የሚያካሂዱት ቤት ለቤት እንደሆነ ጠቁመው፤ ወጣቶቹ ቆጠራውን ሲጀምሩ በየደረጃው ያለው አመራር አባላትና አርሶ አደሩ ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱም ተመልክቷል።