ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች በብዛትና በአይነት ለማስፋት እየሰራች ነው - አምባሳደር ተፈራ ደርበው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች በብዛትና በአይነት ለማስፋት እየሰራች እንደምትገኝ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የንግድ አገልግሎት ሁነት በቤጂንግ ተካሄዷል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው የንግድ ሁነቱን፣ የኢትዮጵያና ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነትን አስመልክቶ ከቻይና ግሎባል ቴሌቪዥን ኔትወርክ (ሲጂቲኤን) ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በሁነቱ ላይ የቱሪዝም ሀብቶቿንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማስተዋወቋንና በቻይና በዘርፉ ከተሰማሩ አጋሮች ጋር ትስስር መፍጠር መቻሏን ገልጸዋል።

የቻይና የቱሪዝም ተዋንያን በኢትዮጵያ በመስኩ ለመሰማራትና ከኢትዮጵያውያን ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በሁነቱ ላይ ባዘጋጀችው የንግድና ቱሪዝም ፎረም ላይ በርካታ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነትና ሁኔታዎች የማይለዋውጠው ስትራቴጂካዊ ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

የበይነ መረብ የንግድ አገልግሎት ከትብብር ዘርፎቹ አንዱ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ በዚህ ረገድም ሁለቱ አገራት የተለያዩ የማዕቀፍ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን አውስተዋል።

አገራቱ ድንበር ተሻጋሪ የሸቀጦችና አገልግሎቶች የበይነ መረብ ግዢና ሽያጭ (ኢ -ኮሜርስ) አማራጭን ለመጠቀም እየሰሩ እንደሚገኙ ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

ሶስት የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮጵያ የበይነ መረብ ንግድ መገበያያ እንዲከፍቱ ፈቃድ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የመገበያያ አማራጩ ምርቶችና አገልግሎቶቿን ማስተዋወቅና ለቻይና ደንበኞች ምርቶቿን መሸጥ እንደሚያስችላት በመጥቀሰ።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ወደ ቻይና የምትልካቸውን የምርት ዓይነቶች ለማስፋት እየሰራች እንደምትገኝ ነው አምባሳደር ተፈራ የገለጹት።

ቡና በቻይና በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈለግ ምርት መሆኑንና የኢትዮጵያ ቡና የሚጠቀሙ ወጣት ቻይናውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱንም አመልክተዋል።

ከቡና ውጪ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ አደንጓሬና ሌሎች የግብርና ምርቶች ወደ ቻይና እንደሚላኩም ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያን ካሳቫን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለመላክ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ አቮካዶ ወደ ቻይና ገበያ ለመላክ ከሀገሪቱ የቁጥጥር ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በዚህም ወደ ቻይና የምትልካቸውን ምርቶች በብዛትና በአይነት ለማስፋት እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ 1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም