ኢትዮጵያና ኩዌት በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ኩዌት በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያና ኩዌት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ (ዶ/ር) ከኩዌት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም ዓቀፍ ትብብር ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ሃማድ አል ማሻን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የሁለቱን ሃገራት የሁለትዮሽና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
አገራቱ ለረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ትብብብር እንዳላቸው በውይይቱ ላይ ተነስቷል።
በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሰኢድ ሙሁመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ኩዌት በግብርና፣ በምግብ ዋስትናና የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮችን ጨምሮ በሌሎች የልማት ዘርፎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አምባሳደሩ አገር በቀል የሆኑ የተራድኦ ድርጅቶች በኩዌት ውስጥ ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው መንቀሳቀስ እንዲችሉና አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።
የኩዌት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የልማትና የዓለም ዓቀፍ ትብብር ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ሃማድ አል ማሻን በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ጠንካራ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
አምባሳደር ሃማድ ከሚሲዮኑ ጋር በቅርበት በመስራት ሕጋዊ ሰውነት ለሚያስፈልጋቸው የተራዶኦ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ኢዜአ በኩዌት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።