የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017(ኢዜአ):- የዓለም የቱሪዝም ቀን ከመስከረም 7 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ቀኑን በማስመልከት በአድዋ ድል መታሰቢያ ሁነት ማዘጋጀቱን ጠቁሟል።
በሁነት ዝግጅቱ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ እንደሚሆንም አመልክቷል።
የተለያዩ የኢጋድ አባል ሀገራት፣ክልሎችና የቱሪዝም ተዋንያን የሚሳተፉበት "Origins travel market" የተሰኘ ኤግዚብሽን እንደሚካሄድ ተጠቅሷል።
የምስራቅ አፍሪካ የ10 አመት የቱሪዝም ማስተር ፕላን ይፋ ይሆናል ተብሏል።
በዝግጅቱ ላይ ለመሳተፍ የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም ሚኒስትሮች ጨምሮ ከ100 በላይ ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ዜጎች ኤግዚቢሽኑን እንዲጎበኙና በሁነቶቹ ላይ እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።
የዓለም የቱሪዝም ቀን እ.አ.አ ከ1980 አንስቶ መስከረም 17 እየተከበረ ይገኛል።