ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እያበረከተ ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2017(ኢዜአ):- ህዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እያበረከተ ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

1ሺህ 499ኛው የነብዩ ሙሀመድ ልደት መውሊድ በዓል በታላቁ አኑዋር መስጂድ በድምቀት ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም ሼህ በድረዲን እና ሌሎች የኃይማኖት አባቶች በበዓሉ ላይ በመታደም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

ሼህ አብዱልከሪም ሼኸ በድረዲን በዚሁ ጊዜ፤ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ነብዩ መሀመድ ያከናወኑትን መልካም ተግባራትና አስተምሮ መሰረት በማድረግ ለሀገርና ለህዝብ በሚጠቅም አርያነት ያለውን መልካም ስራ በማከናወን ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በህዝቦች መካከል የመደጋገፍ ባህል እንዲጎለብትና ሀገራዊ አንድነት እንዲጠናከር ህዝበ ሙስሊሙ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማፋጠን ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳይ ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዜዳንት ሼህ ፈቱውዲን ሃጂ ዘይኑ የዘንድሮው መውሊድ "የሠላሙ ነብይ" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መከበሩን ገልጸዋል፡፡


 

በዓሉም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት ጋር በማስተሳሰር እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮውን የመወሊድ በዓል የነብዩ ሙሀመድ አስተምሮት እና ተምሣሌት የህዝቦች ሠላምና አብሮነት ለማጎልበት በሚያስችል መልኩ በመከበሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ በታላቁ አንዋር መስጂድ በመገኘት ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች በበኩላቸው ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር ሃይመኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እርስ በርስ በመደጋገፍ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አቶ አብዱረህማን ሲራጅ እና ኢክራም መሀመድ ህዝበ ሙስሊሙ የነብዩ ሙሀመድን አስተምሮ መሰረት በማድረግ ለሰላም፣ አብሮነትና እርስ በርስ መረዳዳትን ባህል ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ አቶ አደም ነጋሽ፤ በዓሉን አብሮነትና ሰላምን በሚያጎለብቱ ተግባራትና አቅመ ደካማ ወገኖችን በማገዝ ማክበር እንደሚገባ ነው የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም