ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዘወትር መሻት ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ አግባብ የውሃ ሃብቷን ተጠቅማ ልማቷን ማረጋገጥ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የዘወትር መሻት ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ አግባብ የውሃ ሃብቷን ተጠቅማ ልማቷን ማረጋገጥ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ፤ ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሃብቶች ተጠቅማ ልማቷን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ደግሞ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን መሰረት በማድረግ የኃይል ፍላጎቷን ለማሟላት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የውሃ ሃብቷን ለመጠቀም እያከናወነች ያለው ስራ ተጠቃሽ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የዘወትር መሻትም ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ አግባብ የውሃ ሃብቷን ተጠቅማ ልማቷን ማረጋገጥ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ልማቷን ከማረጋገጥ ውጪ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ለዚሁ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶችም ግድቡ ቀጠናውን በልማት የሚያስተሳስር የትብብር ማዕከል መሆኑን አጽኖት ሰጥተው መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርሆችንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ጽኑ አቋም እንዳላት ጠቅሰዋል

ነገር ግን በአባይ ወንዝ ላይ የቀኝ ግዛት ውሎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ከመሰረቱ ተቀባይነት እንደሌለው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ 

የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለማስቆም የሚከናወን የትኛውም እንቅስቃሴ ተገቢነት የሌለውና የማይሳካ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም