መውሊድ - የአብሮነትና የሰላም ተምሳሌት

መውሊድ አል-ነቢ፣ መውሊድ አን-ነቢ፣ መውሊዲ ሸሪፍ፣ ሚላድ፣ ኢድ ሚላድ ኡን ነቢ፣ ኢድ አል-መውሊድ …ይህ ሁሉ የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) የልደት ቀን መጠሪያ ነው። መውሊድ የሚከበረው በረቢዓል አወል ወር በ12ኛው ቀን አንዳንድ ሀገራት ደግሞ በ17ኛው ቀን መሆኑ ይነገራል።

መውሊድ በመኖሪያ ቤት፣ በመስጊድና በታላላቅ እስላማዊ ማዕከላት ነብዩ በተወለዱበት በረቢየል አወል ወር አሥራ ሁለተኛው ቀን፣ ወይም ነብዩ በተወለዱበት ወር ውስጥ በሚገኝ ሰኞ፣ ወይም በማንኛውም ወር በሚገኝ ሰኞ ቀን ይከበራል።

ዘንድሮም 1 ሺህ 499ኛው የነብዩ መሐመድ (ሰዐወ) ልደት (መውሊድ) በዓል በትውፊቱ መሠረት በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶች “የሰላሙ ነብይ” በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉ ''የሰላሙ ነብይ'' በሚል መሪ ሃሳብ መከበሩ ሰላም ያለውን ከፍተኛ ዋጋ ከማሳየትም በላይ በእስልምና ለሰላም የሚሰጠው ትኩረት ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

በመውሊድ በዓል የነብዩ ታሪክ፣ የእስልምና አመጣጥና ሀዲሶች  ይነበባሉ። በተጨማሪም ቁርዓን በመቅራት፣ የውዳሴ ግጥሞችን በማቅረብ፣ ጣፋጭ ምግቦችን በማዘጋጀትና ለአቅመ ደካሞች ማዕድ በማጋራት እንዲሁም ስጦታ በመለዋወጥ ነው የሚከበረው።

በገጠር የመውሊድ ሥርዓት በአብዛኛው ከሦስት ተከታታይ ቀናት በላይ የሚከበር ሲሆን በተለይ በቀደምት ታላላቅ እስላማዊ ማዕከላት በዓሉ በልዩ ውበት እና ድባብ ይከበራል።

በብዙ አገሮች መውሊድ ሲከበር በጥንት ጊዜ የተጻፉ ሀይማኖታዊ ይዘት ያላቸው የግጥም መጽሐፍት የሚነበቡ ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች ደግሞ በራሳቸው ሊቃውንት የተዘጋጁ የውዳሴ ግጥሞችን በዜማ በማቅረብ በዓሉን ያድምቃሉ።

በግጥሞቹ ውስጥ ስለ ነቢዩ ውልደትና ዕድገት፣ ስለ ቤተሰቦቻቸው ታሪክ፣ ስለተለያዩ አስገራሚ ክንዋኔአቸው፣ ስለ አርቆ አስተዋይነታቸው፣ ስለታላቅነታቸው፣ ስለመጀመሪያው ራዕይ፣ ስለ ቀደምት ተከታዮቻቸው፣ ወዘተ ይዳሰሳል።

መውሊድ ሲከበር ሰደቃ አለ፤ በዚህም ሀብታምና ድሃ ይገናኛሉ፤ የፈጣሪን ውዴታ በምጽዋዕት ከማግኘት ባሻገር የማኅበራዊ ግንኙነትና ትስስር ይጠናከራል። መውሊድ ወንድማማችነትና አብሮነት የሚያንፀባርቅበትም ነው።

መውሊድ መንዙማ በስፋት ከሚተገበርባቸው በዓላት አንዱ ነው። መውሊድና መንዙማ ጥብቅ ትስስር አላቸው። መንዙማ ማመስገን ወይም ማወደስ ማለት ነው። ይዘቱም ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች ገድላቸውና ተዓምራቸው የሚነገርበት፣ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው።

በኢትዮጵያ እነዚህ የመውሊድ ክንዋኔዎች በትግራይ ነጃሽ፣ በሆጂራ ፎቂሳ፣ በሰሜን ወሎ ዳና፣ በደቡብ ወሎ ጃማ ንጉሥ፣ በባሌ በድሬ ሸኽ ኹሴን፣ በጅማ በቁባ አባረቡ፣ በደንግላ እና በሌሎችም አካባቢዎች በስፋት ይከናወናሉ።

የዘንድሮ ዓመት የመወሊድ በዓል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የተቋቋመበት 50ኛ ዓመት በዕለተ መውሊድ በመሆኑ በዓሉ ድርብ በመሆኑ በተለየ ዝግጅት ነው እየተከበረ የሚገኘው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባልና የመውሊድ በዓል አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሸይኽ አብዱልሐሚድ አህመድ እንደገለጹት፤ የመጅሊሱን 50ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ የመውሊድ በዓል በተለያዩ ስርዓተ ክዋኔ በደማቅ መርሃ ግብር ተከብሯል።

ከዚህም በተጨማሪ የረቢዕል አወል ወር እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚሰጡ ትምህርቶችና ደዕዋዎች (ስብከቶች) “የሰላሙ ነቢይ፡” ከሚል መሪ ሃሳብ እንዲሆን በምክር ቤቱ የመውሊድ ዓቢይ ኮሚቴ ውሳኔ ተላለፎ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

በዚሁም መሰረት የሰላም ግንባታ ሥራዎችን በመደገፍ፤ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በማድረግ ህዝበ ሙስሊሙ አስተዋጽኦውን አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችለውን ብርታትና ቁርጠኝነት የሚሰንቅበት በዓል ሆኖ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል።

የሰላምና የአብሮነት ምልክት ለሆነው ለዚህ መልካም ዓላማ መሳካት ያለ ልዩነት በጋራ በመተሳሰብ፤ በእዝነት የነብዩን መልካም ስራዎች መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።

የሃይማኖቱ አባቶችም ከመዕመኑ ጋር በመሆን በጸሎት፣ ቁርዓን በመቅራትና ሐዲሶችን በማንበብ ለሀገር ሰላምና ለህዝቦች አንድነት መጸለይና በማስተማርን የየዕለት ተግባራቸው ሊያደርጉት እንደሚገባ አንስተዋል።

በርግጥም የዘንድሮው የመውሊድ በዓል ድርብ በዓል ነው። መጅሊስ የተቋቋመው የዛሬ 50 ዓመት በመውሊድ ዕለት ነበርና። መልካም በዓል!


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም