ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሰረቱ ለማስተካከል ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2017(ኢዜአ):- በመዲናዋ የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሰረቱ ለማስተካከል ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ለውጥ እያመጡ መሆኑንም ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወንድሙ ኡመር ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይ የትምህርት ደረጃዎች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መሰረት የሚጥሉ ናቸው፡፡

ከዚህ አኳያ በመዲናዋ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለተማሪዎች ሳቢና ማራኪ እንዲሆኑ ከማድረግ ጀምሮ መምህራንን የማሰልጠንና የማብቃት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህም የትምህርት ጥራት ችግርን ከመሰረቱ ለማሻሻልና በስነ ምግባር የታነጸ ብቁ ትውልድ ለማፍራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በመዲናዋ የተጀመረው የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሰፊ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ተናግረዋል።

ከ14 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራንን በጨዋታ ላይ የተመሰረተ የማስተማር ስነ ዘዴ በማሰልጠን የማብቃት ስራ መሰራቱንም ነው የተናገሩት፡፡

ከፍተኛ የተማሪዎች ቁጥር ጥምርታ ያለባቸውን ትምህርት ቤቶች በመለየት ተጨማሪ ክፍል መገንባትን ጨምሮ ለ2017 ትምህርት ዘመን ከስምንት በላይ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን መገንባት መቻሉንም ነው የተናገሩት፡፡

በመዲናዋ 223 የቅድመ አንደኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶችና 906 የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም