መውሊድን በአብሮነትና በመረዳዳት እያከበርን ነው -በደቡብ ወሎ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች - ኢዜአ አማርኛ
መውሊድን በአብሮነትና በመረዳዳት እያከበርን ነው -በደቡብ ወሎ የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች
ደሴ ፤ መስከረም 5/2017(ኢዜአ)፡- የመውሊድ በዓልን በአብሮነትና በመረዳዳት እንዲሁም በፍቅርና በአንድነት እያከበርን ነው ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ገለጹ።
አንድ ሺህ 499ኛው የመውሊድ በዓል በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ነው።
በዞኑ በቃሉ ወረዳ የገታ መስጅድ የሐይማኖት አባት ሸህ ኡመድ ሃጂ ሙህዲን ለኢዜአ እንደገለጹት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡ የእመነቱ ተከታዮች ጋር በዓሉ በአንድነትና በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዓሉ ሐይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ የታላቁን ነብይ የህይወት ታሪክ በማውሳት፣ አስተምሯቸውን በማስታወስ፣ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ያላቸውን ክብር፣ እዝነት፣ ደግነትና ሌሎችንም ባህሪያቸውን በማስተማር ጭምር እየተከበረ እንደሆነ ገልፀዋል።
መስጅዱ ታሪካዊና ጥንታዊ መሆኑንም ጠቁመዋል ።
በዓሉን በገታ መስጅድ ለማክበር ከድሬደዋ ከተማ መምጣታቸውን የተናገሩት ሸህ ሰይድ አሊ በበኩላቸው፤ በታሪካዊ ስፍራው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በማክበራቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ታላቁን በዓል አንድነታችንንና ሰላማችንን በመጠበቅ በአብሮነትና በመረዳዳት እያከበርነው ነው ብለዋል።
በዓሉን በመስጅዱ በፍቅርና በአንድነት ማክበር ጀምረናል ያሉት ደግሞ የባቲ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ ናቸው።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አሊ ይማም በቃሉ ወረዳ ገታ መስጆድና በኮምቦልቻ ከተማ መጂት መስጅድ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።
ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ የመረዳዳት ባህሉን በማጎልበት መሆን እንዳለበት ገልፀዋል።
የነብዩ መሃመድ /ሰ.ዐ.ወ/ አስተምህሮ ሰላም፣ አብሮነት፣ ፍቅርና እኩልነት ነው ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው በበዓሉ ይህንኑ በተግባር ማሳየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዓሉ የአንድነት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመረዳዳት ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ አስያ ኢሳ ናቸው።
በተለይ በዓሉ ሲከበር የተቸገሩትን ወገኖች በመርዳት የነብዩን እዝነት፣ አቃፊነት፣ ደግነት፣ አብሮትና ሌሎችንም ስብዕና በመላበስ ሊሆን ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በበዓሉ በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች በሚገኙ መስጅዶች እየተከበረ ነው።