ቀጥታ፡

መድረኩ አመራሩን ሀገራዊ፣ቀጠናዊ እና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል ነው- አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017 (ኢዜአ)፡- ከፍተኛ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የአቅም ግንባታ መድረክ በዋናነት አመራሩን ሀገራዊ፣ቀጠናዊ እና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ከ2ሺህ በላይ ከፍተኛ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት የአቅም ግንባታ መድረክ "የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው እለት በአዳማ ከተማ መጀመሩን ገልጸዋል።

መድረኩ በዋናነት አመራሩን ሀገራዊ፣ቀጠናዊ እና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለዚህም በስልጠናው ላይ ተግባራዊ በሚደረጉ የሰነድ ገለፃዎች፣የቡድን ውይይቶች፣የሀይል መድረኮች እና ምላሾች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በአመራሩ ዘንድ እንዲፈጠር ስልጠናው በር ከፋች እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።

አመራሩ ከሚቀስመው እውቀት በተጨማሪም በሚኖሩ የልምድ ልውውጥ እና የቡድን ውይይት መድረኮች ፓርቲውን እና መንግስትን የሚያጠናክሩ ግብአቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እንድናገኝ ስልጠናው እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ቀን ውሎም በብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የቀረበው በሕዝቦች ትስስር፣በዜጎች ክብር፣በሰብአዊ ብልፅግና እና በሀገራዊ ልዕልና ላይ መሰረት አድርጎ እንዲገነባ የምንፈልገው የኢትዮጵያ ህልም ላይ ሰፊ ገለፃ ቀርቦ የጋራ መግባባት የጨበጥንበት ነውም ብለዋል።

በቀጣይ ቀናትም በሚቀርቡ የተለያዩ ይዘቶችን ባዘሉ ገለፃዎች የብሔራዊነት ትርክትን ለማስረጽ፣ የሪፎርም ሥራዎቻችንን ይበልጥ ውጤታ ለማድረግ፣ የማስፈፅምና የመፈፀም ብቃትን ለማሳደግ በአጠቃላይ ህልማችንን ለማሳካት የሚያስችሉ ሀገራዊ ቁልፎችን በጋራ የምንጨብጥበት እንደሚሆን ያለኝን እምነት ለመግለፅ እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም