ቀጥታ፡

ለግብርና ቆጠራ እና ጥናት የሚጠበቅባቸውን  ሀላፊነት እንደሚወጡ መረጃ ሰብሳቢዎች ገለጹ

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 4/2017 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዘንድሮ ለሚካሄደው የግብርና ቆጠራ እና ጥናት የሚጠበቅባቸውን  ሀላፊነት ለመወጣት  እንደሚሰሩ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ መረጃ ሰብሳቢዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዘንድሮ ለሚያካሂደው የግብርና ቆጠራ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለድሬዳዋ አስተዳደር እና ለሐረሪ ክልል የመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

ሰልጣኞቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሄደው የግብርና ቆጠራና የናሙና ጥናት ተገቢውን የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ክህሎት እያገኙ ነው።

ከሐረሪ ክልል የመጣው ሰልጣኝ ወጣት አቤል መንገሻ፤ በተሰጣቸው የተግባቦት፣ የቴክኒክ እና የቴክኖሎጂ ዕውቀት እና ክህሎት በመታገዝ የተጣለባቸውን  ኃላፊነት ለመወጣት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግሯል።


 

ሌላኛው የድሬዳዋ  ሰልጣኝ  ወጣት  ኢድሪስ አብደላ እንዳለው፤  በአገሪቷ የሚካሄደው የግብርና ናሙና ጥናት አገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል ለምታደርገው ግስጋሴ መጠናከር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ተረድቷል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እየወሰዱት ያለው ስልጠና ይህን ታላቅ  ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚያስችለውም ነው የገለጸው።


 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ግርማ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ዘንድሮ በመላው አገሪቷ ለግብርና ፓሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ቆጠራ እና ጥናት ይካሄዳል።

ጥናቱ በግብርና የለውጥ ጉዞ ላይ ከፍተኛ እና ተጨባጭ ለውጥ የሚያስገኝ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል ግብርናው ተጠቃሽ መሆኑን አቶ ሙሉጌታ አመልክተዋል።

እነዚህ የተገኙ ለውጦች በመረጃ እና በማስረጃ በማስደገፍ ጉዞውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚካሄደው ጥናት አበርክቶት የላቀ ነው ብለዋል።

የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ መረጃ ሰጪው ህብረተሰብ ለመረጃ ሰብሳቢዎች ተባባሪ መሆን እንዳለበት አመልክተው፤ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለጥናቱ ስኬታማነት  የድርሻቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ የግብርና ቆጠራ እና ጥናት በዋናነት በሰብል ምርት እና በእንስሳት እርባታ ላይ አተኩሮ የሚካሄድ ነው።

ለዚህ ቆጠራና ጥናት የሚሳተፉ ቁጥራቸው 43 ሺህ የሚጡጉና የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ወጣቶች በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና በመውሰድ ላይ ናቸው።

ወጣቶቹ ከተያዘው መስከረም ወር ጀምሮ ወደመስክ ተሰማርተው መረጃ የሚያሰባስቡ ሲሆን ጥናቱም ለሀገሪቱ የግብርና ዕቅድና ፖሊሲ የጎላ አስተዋጾ እንደሚኖረው ታውቋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም