ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ ከፋብሪካዎች የሚወጡ ምግቦች በንጥረ ነገር የበለጸጉ መሆናቸውን አረጋግጦ ሊጠቀም ይገባል 

አዲስ አበባ፤መስከረም 4/2017(ኢዜአ)፦ኅብረተሰቡ ከፋብሪካዎች የሚወጡ ምግቦች በንጥረ ነገር የበለጸጉ መሆናቸውን ማረጋገጥና ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት ሊከተል እንደሚገባ የሥነ-ምግብ ባለሙያዎች ገለጹ።

ሥርዓተ-ምግብ የጤና የልማት አንዱ ወሳኝ አካል መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

የተመጣጣነ ምግብ መመገብ ጤናማና ትክክለኛ ሰውነት ለመገንባት፣ ጠንካራ የበሽታ መቋቋም አቅም ለመፍጠር፣ እናቶች ጤናማ እርግዝና እንዲኖራቸው ለሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የመጋለጥ እድልን እንደሚቀንስና ረጅም እድሜ ለመኖር እንደሚያስችልም ተገልጿል።

ንጥረ-ምግብ፤ በምግብ ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ሲሆኑ ለሰውነት ኃይል፣ ለሕዋሶች መታደስ፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኙ ቅመሞች በትክክል እንዲሰሩና ትክክለኛ የሰውነት እድገት እንዲኖር ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ በምግብ ውስጥ የሚገኙ ንጥረ-ነገሮች ሲሆኑ ሁለት አይነትም ንጥረ ምግቦች አሉ። 

ዋና ንጥረ ምግቦች (Macro Nutrients) ለሰዉ ልጆች የዕለት ከእለት እንቅስቃሴና እድገት የሚያግዙ የምግብ ንጥረ ነገር ዓይነቶች ሲሆኑ በዋናነት ኃይልና ሙቀት ሰጭና ገንቢ የንጥረ-ምግብ ዓይነቶች ሲሆኑ እነዚህም ካርቦኃይድሬት፣ ፕሮቲንና ቅባትን ያካትታል። 

ደቂቅ ንጥረ ምግቦች (Micro Nutrients)፡- በአነስተኛ ደረጃ በየዕለቱ የሚያስፈልጉ ወሳኝ ንጥረ ምግቦች ሲሆኑ ጤናማ የሰውነት እድገት፣ የበሽታ መከላከል አቅምን የሚያጎለብቱና የምግብ መፈጨትን የሚያፋጥኑ ቫይታሚንና ማዕድናትንም ይጨምራል።  

እነዚህን የሚያገኝ ህጻን ትምህርት የመቀበል አቅሙ ይጨምራል፤ በተለይም የተመጣጠነ ምግብ የሚጠቀሙ ሰዎች ምርታማና በሂደትም የድኅነት ቀንበርን ለመስበር የሚያስችል እድል ያላቸው ሲሆን ያልተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙ ደግሞ መቀንጨርን ጨምሮ ለከፋ የጤና ችግር ይጋለጣሉ።

ይህም አንደኛ በምርታማነትና ከፍ ሲልም በእድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብ ማበልጸግ አማካሪ ሽብሩ ቀልቤሳ የሥርዓተ-ምግብ መጓደል በትምህርት አቀባበል፣ በምርታማነት እንዲሁም በኢኮኖሚው እድገት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያሳደረ ነው ብለዋል።


 

በሥርዓተ-ምግብ ላይ የሚሰራውና በዚህ ሳቢያ ችግር የደረሰባቸውን እየደገፈ የሚገኘው የስፓይናል ቤፊዳና ኃይድሮ ሴፋሊስ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት መሥራች ቤዛ በሻህ ችግሩ ከኢኮኖሚ ባለፈ የማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ውስብስብ ችግሮችን እንደሚያስከትል ገልጸዋል።

እንደ ሽብሩ ቀልቤሳ ገለጻ በስፋት ከነዚህ ጥቃቅን ንጥረ ነገሮች እጥረት የሚከሰተው አንዱ ችግር ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ጋር መወለድ መሆኑን ጠቁመው ይህም በዋናነት ፎሊክ አሲድ ከተሰኘው ንጥረ ነገር መጓደል ጋር የተያያዘ ነው።

ይህ ንጥረ ነገር የሰውነት ሕዋሳት በአግባቡ እንዲራቡ፣ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በአግባቡ ቦታቸው ላይ ተሰካክተው ልጅ እንዲፈጠር የሚያደርጉ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የፎሊክ አሲድ ንጥረ ነገር አለመኖር ጋር በተያያዘ ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ጋር መወለድ፣ በጭንቅላት ውስጥ አላስፈላጊ ውኃ መከማቸት  አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የዓለም ጤና ድርጅት አንድ እናት ለመውለድ ካቀደች ከ ሁለት ወራት በፊት ይህንን የፎሊክ አሲድ እንክብል መውሰድ እንዳለባት  ያዛል ያሉት አቶ ሽብሩ አሁንም ለመውለድ የተዘጋጁ በጤና ተቋማት በሚታዘዝላቸው መሰረት ይህንን እንክብል መውሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።  

እንዲሁም ሌላኛው የቫይታሚን ኤ እጥረት መሆኑንና ይህም ለአይነ ስውርነት የሚያጋልጥ መሆኑን ገልጸው፥ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ የቫይታሚን ዲ እጥረት እየታየ መምጣቱን ጠቁመዋል።

 

የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል የምግብ ማበልጸግና የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምርና ልማት ዴስክ ኃላፊ ሶፎንያስ ምንደሲል የሥርዓተ-ምግብ መዛባትን ለመቅረፍ ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

እነዚህን ለመቅረፍም በአመጋገብ ስብጥር (diet diversification) እንክብሎችን ወይም ልዩ የምግብ ዓይነቶችን መጠቀም (Suplimentation) እና የምግብ ማበልጸግ (fortification) ላይ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምግብ ማበልጸግ እነዚህ ለምግብነት የሚውሉ ምርቶችን አስፈላጊውን ንጥረ ነገሮች በመጨመር የማበልጸግ ሂደት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም