የመውሊድ በዓል ሲከበር የታላቁን ነብይ መልካም ስብእና ደግነት ፍቅርና እዝነት በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017(ኢዜአ)፦የመውሊድ በዓል ሲከበር የታላቁን ነብይ መልካም ስብእና ፍቅርና እዝነት በመሰነቅ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶችን በተግባር በማሳየት ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ።

1 ሺህ 499ኛው የነብዩ መሀመድ ልደት /መውሊድ/ ነገ መስከረም 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የመውሊድ ክብረ በዓል በትውፊቱ መሠረት የነብዩን ስራዎች በማውሳት “የሰላሙ ነብይ” በሚል መሪ ሃሳብ  በታላቁ አንዋር መስጅድ ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል።

አከባበሩን በሚመለከት ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የኢማን አባስ መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ ሲራጅ፤ የነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) መውሊድ በእስልምና ትልቅ ስፍራ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የእርሳቸው ወደ ዚህች ምድር መምጣት የብዙ ነገሮች መሰረትና የስኬት መንገድ የገለጠ ስለመሆኑ ጠቅሰው ከእርሳቸው ፍፁም ደግነት ፍቅርና እዝነት የተማርንበት ነው ብለዋል።

የመውሊድ በዓል ከታላቁ ነብይ መልካም ስብዕናን፣ ቸርነትን፣ ደግነትን፣ ለሰው አሳቢነትን፣ ርህራሄና ሌሎችንም መልካም ስራዎቻቸውን የምናስታውስበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም የመውሊድን በዓል ስናከብር የታላቁን ነብይ መልካም ስብእና ፍቅርና እዝነት በመሰነቅ የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቶችን በማስቀጠል መሆን አለበት ብለዋል።

ሁላችንም የእሳቸውን መልካምነት በመላበስ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በማገዝ፣ ሰላም ፍቅርና እዝነትን በተግባር በማሳየት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም