ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ቻይና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ቻይና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

የቻይና አምራች ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለመመልከት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም ተጠቁሟል።

የብሪክስ አጋርነት ለአዲሱ የኢንዱስትሪ አብዮት ውይይት በቻይና ፉጂያን ግዛት ሺያሜን ከተማ ላይ ተካሄዷል። ኢትዮጵያ በውይይቱ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።

ከመድረኩ ጎን ለጎን የኢትዮጵያና ቻይና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተቋማትም ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ተገኝተዋል።


 

በውይይቱ ከሁለቱም አገራት ከአምራች ኢንዱስትሪ የተወጣጡ የዘርፉ ተዋንያን የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

የልምድ ልውውጡ የቻይና አምራች ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች በመመልከት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያግዛቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አምራች ባለሃብቶችም የቻይና የኢንቨስትመንት አማራጭ በማየት የዘርፉ የኢንዱስትሪ ተዋንያን ትስስራቸውን ለማጠናከርና የቻይናን የኢንዱስትሪ አብዮት ልምድ ለመቅሰም እንደሚያስችላቸው ተጠቁሟል።

የብሪክስ አጋርነት ለአዲሱ የኢንዱስትሪ አብዮት ውይይት የኢንዱስትሪ ልማት ትብብር አገልግሎቱን ለማጠናከርና አባል ሀገራቱ የሚደጋገፉበትን የኢንዱስትሪ አቅም እንደሚፈጥር ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም