የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል አሜሪካን ጨምሮ በሁሉም ክፍላተ አህጉራት ቅርንጫፎችን ይከፍታል - የማዕከሉ ቦርድ ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል አሜሪካን ጨምሮ በሁሉም ክፍላተ አህጉራት ቅርንጫፎችን ይከፍታል - የማዕከሉ ቦርድ ሊቀመንበር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017(ኢዜአ):- ዋና ቢሮውን አዲስ አበባ ያደረገው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል አሜሪካን ጨምሮ በሁሉም ክፍላተ አህጉራት ቅርንጫፎችን እንደሚከፍት አስታወቀ።
ለማዕከሉ መጠናከር በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል ተቀማጭነታቸውን እንግሊዝ ባደረጉ በታሪክ፣ ሕግ፣ ባሕል እና በሌሎች ሙያዎች ሰፊ ልምድ ባካበቱ አሳቢያን የተወጠነ ድርጅት ነው።
ትኩረቱን በታሪክ፣ ቅርስ እና ትምህርት ላይ ያደረገው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ማዕከል ሕዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ በተካሄደ ስነ ስርዓት ነበር ዋና ፅህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ የከፈተው።
ማዕከሉ በቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ፕሬዝዳንትነት፤ በቀድሞው የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ዴቪድ ፍራንሲስ የቦርድ ሊቀመንበርነት እና የታዋቂው የፓን-አፍሪካኒዊነት አቀንቃኝ ማርክስ ጋርቬይ ልጅ በሆኑት ጁሊየስ ጋርቬይ (ዶ/ር) የበላይ ጠባቂነት ይመራል።
የማዕከሉ የቦርድ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዴቪድ ፍራንሲስ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ማዕከሉ ከተቋቋመ ጀምሮ እስካሁን ወሳኝ ምዕራፎች አልፏል።
ማዕከሉ ጽህፈት ቤቱን ከከፈተ በኋላ ሕጋዊ ሰውነት የማግኘትና አደረጃጀት የመዘርጋት ሂደቶችን ያጠናቀቀ ሲሆን በአድዋ ድል መታሰቢያ የተከፈተውን ፅህፈት ቤቱን በቅርቡ ወደስራ እንደሚያስገባ ጠቁመዋል።
ማዕከሉ በአዲስ አበባ የተመሰረተው ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት ትግል አርዓያ መሆኗንና እና ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ የነበራትን አይተኬ አበርክቶ ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ አንስተዋል።
ማዕከሉ ዋና ቢሮውን አዲስ አበባ ቢያደርግም በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ቅርጫፎችን እንደሚከፍት ገልጸዋል።
ለአብነትም የማዕከሉ ምክር ቤት የበላይ ጠባቂ በሆኑት ጁሊየስ ጋርቬይ (ዶ/ር) አስተባባሪነት በአሜሪካ ቅርንጫፉን እንደሚከፍት ገልጸው በጀማይካና በሌሎችም አገራት ቅርንጫፍ የመክፈት ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለማዕከሉ ዕውን መሆን ያደረገው ትብብርና ድጋፍ አይተኬ መሆኑን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን አመስግነዋል።
ማዕከሉ ከወራት በኋላ የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት ከአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እና ከዝክረ-አድዋ ድል ክብረ በዓል ጋር በማጣጣም በድምቀት እንደሚያከብርም ተናግረዋል።
ማዕከሉ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ባህልና ትምህርት ላይ አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀው፤ የትናንትንት ታሪክን በቅጡ በመተረክ የነገ ትውልድን በተሻለ መሰረት ለይ ለመገንባት አስቻይ ተግባራት ያከናውናሉ ብለዋል።
ተዛብቶ የተተረከውን የጥቁሮች ታሪክ፣ ባህል እና ትርክት አፍሪካዊያን በራሳቸው ስልትና ቋንቋ እንዲጽፉ፣ ሃሳባቸውን እንዲያንሸራሽሩ እና ለትውልድ እንዲሰንዱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የጥቁር ሕዝብ አኩሪ ገድል ከሆኑት ታሪኮች መካከል አደዋ ድል አንዱ መሆኑን በመጥቀስ፤ አድዋና መሰል የአፍሪካዊያን ታሪኮች በቅጡ መተረክ፣ ባሕላቸውን ማስተዋወቅ እና ማስተማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ማዕከሉ ጽህፈት ቤቱን በአድዋ ድል መታሰቢያ ጋር ያስተሳሰረው አድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ህዝብ ታሪክ መሆኑን በማሰብ ስለመሆኑም አንስተዋል።
ተንሸዋሮ የተተረከውን አፍሪካዊያን ታሪክ ዳግም አስተካክሎ ለመተረክ በዓለም የሳይንስ የትምህርትና ባህል ድርጅት ድጋፍ የአፍሪካ አጠቃላይ ታሪክ የመጻፍ ስራዎች እንደተጀመሩ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በቅኝ ገዥዎች ተዘርፈው በየክፍላተ ዓለሙ ተበታትነው የሚገኙ የጥቁር ህዝቦች ታሪካዊ አሻራ የሚዘክሩ ቅርሶችን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ማስመለስ ሌላው የማዕከሉ ወሳኝ ተግባር መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ 'ፀሐይ' አውሮፕላን ጨምሮ ከተለያዩ አውሮፓ ሀገራት የሚገኙ አንጡራ ቅርሶቿን እያስመለሰች መሆኗን በአርዓያነት የሚወስድ እንደሆነ አድንቀዋል።
የዓለም ጥቁር ሕዝበች ማዕከል የአፍሪካዊያን ታሪክ በየሀገራቱ ስርዓተ ትምህርት እንዲካተት በማስቻል የበይነ-አፍሪካዊያን ትስስር ማጠናክርና ፓን-አፍሪካዊነትን እንዲጎልብት ይሰራም ብለዋል።
ማዕከሉ መላው ጥቁሮችን ያካተተና ያማከለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች በራሳቸው ባህል፣ ታሪክና ትምህርት ላይ ለሚሰራው ማዕከል ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።