የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2024/25 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ ክለብ ጋር ያከናውናል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።

በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያው የዩጋንዳውን ቪላ ክለብ በደርሶ መልስ ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፉ ይታወቃል።

በአሰልጣኝ ልዑል ሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለጨዋታው በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። የመጨረሻ ልምምዱንም ትናንት በአበበ በቂላ ስታዲየም አከናውኗል።


 

ተጋጣሚው ያንግ አፍሪካንስ በመጀመሪያው ዙር የብሩንዲውን ቪታሎ ክለብ በአጠቃላይ ውጤት 10 ለ 0 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር መቀላቀሉ ይታወቃል።

በ57 ዓመቱ አርጀንቲናዊ ሚጉዌል አንጌል ጋሞንዲ የሚሰለጥነው ያንግ አፍሪካንስ በታንዛንያ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል። ላለፉት ሁለት ቀናት በአበባ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን አድርጓል።

የ40 ዓመቱ ሴኔጋላዊ ኢሳ ሲ የሁለቱን ቡድኖች ወሳኝ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታ መስከረም 11 ቀን 2017 ዓ.ም ዛንዚባር ላይ ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በደርሶ መልስ ካሸነፈ ወደ ምድብ ድልድል መግባቱን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን የወከለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

ክለቡ በ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም