ዲጂታል መታወቂያ ደህንነቱ የተጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎት ለመዘርጋት ያስችላል -የዘርፉ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል መታወቂያ ደህንነቱ የተጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎት ለመዘርጋት ያስችላል -የዘርፉ ባለሙያዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017 (ኢዜአ):- ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎት ለመዘርጋት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም "የመታወቅ መብት" በሚል መሪ ሃሳብ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም ይከበራል።
የመታወቂያ ቀንን አስመልክቶ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ያሳተፈ የዌብና (በይነ መረብ) ውይይት ተካሂዷል።
በብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤል መሪነት በተካሄደው በዚህ ውይይት ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተገልጿል።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር አብዮት ባዩ እንዳሉት ኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ ቀርጻ ገቢራዊ እያደረገች ሲሆን ብዙ መንግስታዊ አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እየተሰጡ ነው።
ሁሉም ተቋማት የራሳቸውን ዲጂታል አገልግሎት እየዘረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስወገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ለአብነትም በመንግስት ተቋማትና በተገልጋዮች መካከል የተሻለና የተፋጠነ አገልግሎት እንዲሳለጥና በቀላሉ መረጃ ለመለዋወጥ ያግዛል ብለዋል።
ይህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስወገድ ለዜጎች አገልግሎትን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የአካታችነት ስርዓት እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገር ፈጠራን ለማጎልበትም ያግዛል ነው ያሉት።
የአይዲፎር አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ዮሴፍ አቲክ ዲጂታል መታወቂያ ሰው ተኮር ፕሮግራሞች ተደራሽ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ ለመጨመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል አስተዳደርና አገልግሎት ፖሊሲዎች አውጥታ ገቢራዊ ማድረጓን አድንቀው፤ ፋይዳ በመንግስትና በዜጎች ብሎም በባለድርሻ አካላት መካከል የመተማመን ምህዳር ያሰፋል ብለዋል።
የዲጂታል መታወቂያ ማዕቀፍ ተደራሽ፣ ቀጣይነት ያለውና ሃላፊነት የታከለበት የአገልግሎት ስርዓት ለመገንባት እንደሚያስችል ነው ያነሱት።
በዓለም ባንክ የመታወቂያ ለልማት ወይም 'አይ ዲ ፎር ዲ' ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ጁሊያ ክላርክ በበኩላቸው ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመዘርጋት ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይ ሴቶችን ጨምሮ ከማህበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊና ከሌሎችም አገልግሎቶች ተገልለው የቆዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል።