የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት በድሬዳዋ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት በድሬዳዋ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):- የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የኮከቦች ሽልማት እና የማጠቃለያ ፕሮግራም መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም በድሬዳዋ እንደሚካሄድ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
በመርሐ ግብሩ በሰባት ዘርፍ የዓመቱ ኮከቦች እንደሚሸለሙና ለተሳታፊ ክለቦችና ባለሜዳዎች የገንዘብ ክፍፍል እንደሚደረግ ገልጿል።
ኮከብ ተጫዋች፣ ኮከብ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋችና ኮከብ ግብ ጠባቂ ከዘርፎቹ መካከል ይጠቀሳሉ።
ተመልካቾች በአክሲዮን ማህበሩ የቴሌግራም ገጽ ከሰኔ 19 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድምጽ ሰጥተዋል።
ከተመልካቾች ድምጽ በተጨማሪ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና የሊጉን ጨዋታ የቀጥታ ስርጭት መብት የወሰደው የደቡብ አፍሪካው ሱፐር ስፖርት የቴሌቪዥን ጣቢያ በድምጽ አሰጣጡ ተሳትፎ አድርገዋል።
ሽመልስ በቀለ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ፈቱዲን ጀማል፣ ጋናዊው የአማካይ ተጨዋች ባሲሩ ዑመር፣ ቸርነት ጉግሳ፣ ቢኒያም ፍቅሬና ኤርትራዊው አጥቂ አሊ ሱሌማን በኮከብ ተጫዋቾች ዘርፍ በእጩነት የቀረቡ ናቸው።
ወገኔ ገዛኸኝ፣ ተመስገን ብርሃኑ፣ ዮሐንስ መንግስቱ፣ በፍቃዱ አለማየሁ፣ መድን ተክሉና ቢኒያም አይተን ኮከብ ተስፈኛ ወጣት ተጫዋቾች እጩዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ፍሬው ጌታሁን፣ አቡበከር ኑራና ሰዒድ ሀብታሙ የኮከብ ግብ ጠባቂ እጩዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በድሬዳዋ ከተማ መስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጀመር ማህበሩ አስቀድሞ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።