በሚገባን ልክ ያልተጠቀምንበት የቆዳና ሌጦ ሃብት - ኢዜአ አማርኛ
በሚገባን ልክ ያልተጠቀምንበት የቆዳና ሌጦ ሃብት

ኢትዮጵያ በቀንድ ከብቶች ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ቢሆንም ከዘርፉ ማግኘት ከሚገባት ኃብት አንጻር በሚፈለገው ደረጃ እያገኘች እንዳልሆነች መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለዚህም ደግሞ የጥሬ ቆዳ አቅርቦትና ጥራት መጓደል፣ የኬሚካል እጥረት፣ የፋብሪካዎች ሥራ ማቆም እና የመሸጫ ዋጋ መቀነስ ዘርፉ በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ማነቆ ሆነው ከቆዩት መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
በየዓመቱም ከምታመርተው ቆዳና ሌጦ ከግማሽ ያልበለጠው ብቻ ጥቅም ላይ እያዋለች ሲሆን፤ ቀሪው በጥራት ችግርና በሌሎች ምክንያቶች አገልግሎት ላይ የማይውል ነው፡፡
የቆዳው ዘርፍ ያለውን ችግር ስትራቴጂያዊ በሆነ መንገድ ለመፍታትና ዘርፉ ለሀገር ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የ10 ዓመት የቆዳ ልማት ስትራቴጂ መዘጋጀቱም ይታወሳል፡፡
ስትራቴጂው የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን በክላስተር ለይቶ ማደራጀት፣ በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት መሳብ፣ የጥሬ ቆዳና ጥራትን መጨመር፣ እንዲሁም የገበያ አማራጮችን ማስፋትና ሌሎች የመፍትሔ ሃሳቦችን አካቶ መተግበር ጀምሯል፡፡
የኢትዮ-ሌዘር ኢንዱስትሪ /አሊኮ/ ቆዳ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ወሰኑ እንዳሉትም፤ በጥሬ ቆዳ ላይ የሚታየው የጥራት ችግር ከዘርፉ ማነቆዎች መካከል ተጠቃሹ ነው ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ለቆዳ ያለው አመለካከት እንደቀደመው አይደለም የሚሉት ስራ አስኪያጁ ቆዳ በሚታረድበትና በሚሰበሰብበት ወቅት የጥራት ችግሮች ይስተዋላሉ ብለዋል፡፡
በዚህም ኢንዱስትሪዎች የሚያስገቡትን ምርት በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እንዳያወጡ ማነቆ እንደሆነባቸው ጠቁመው ዘርፉ በሚፈለገው መጠን እንዳያድግም እንቅፋት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት የቆዳ ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሚሻሞ ሞካሶ፤ አሁን ላይ ጥሬ ቆዳን ወደ ውጪ ከመላክ እሴት ጨምሮ መላክ ላይ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህም ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ከሚያስገኘው ጠቀሜታ ባሻገር ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ በሀገር ደረጃ የሚመረቱ የቆዳ ውጤቶች ከውጪ ይገቡ የነበሩትን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ አቶ ዳኛቸው አበበ ያለቀላቸውን የቆዳ ውጤቶች የሚያመርቱ በርካታ ኢንዱስትሪዎች መከፈታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ ወደ ውጪ ከሚልኩት ምርቶች ባሻገር ይገቡ የነበሩትን ምርቶች የውጪ ምንዛሪ ከማስቀረት አኳያ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙና ይህንን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እንደ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በቆዳው ዘርፍ የሀገርን ልማት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው፡፡
አሁን ላይ የጸጥታ ኃይሎችን ጫማ እና ሴፍቲ ጫማ የሚባሉት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በመመረት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህም ዘርፉ ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳይ በኩሉን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተማሪ ጫማዎች ፕሮጀክቶትም ተግባራዊ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ይላሉ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ሚሻሞ ሞካሶ፤ በ2017 ከዘርፉ የሚገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚስተዋሉ ችግሮችን የመፍታት ስራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱም ከ130 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡
ለቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪዎች እንደ ግብዓትነት የሚያስፈለጉ ኬሚካሎችን በሀገር ውስጥ የማምረት ሂደቱ ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡