በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ሥርዓቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የትራንስፖርት ሥርዓቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):-የትራንስፖርት ሥርዓቱን የተሳለጠ ለማድረግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው የመስከረም ወር የትምህርት መጀመር ጋር ተያይዞ የሥራ አቅጣጫ ለመስጠትና የ3 ወራት እቅድ ዙሪያ ከተጠሪ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ዳኛቸው ሽፈራው በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ የትራንስፖርት ሥርዓት አገልግሎት የተቀላጠፈ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በተለይም በመስከረም ወር በርካታ በዓላት የሚከበርበትና ትምህርት የሚጀመርበት በመሆኑ የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰራውን ሥራ የበለጠ አጠናክሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በሥምሪቶች ላይ የነገ አገር ተረካቢ ለሆኑ ተማሪዎች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በዚህ ታክሲዎች የተማሪዎች ሰርቪስ መስጠት እንደሚችሉ ገልጸው ነገር ግን ወደ መሥመራቸው ተመልሰው ሕዝቡን ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ የብዙኃን ትራንስፖርት በብዛት ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመው ታክሲዎችን ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑም ይደረጋል ብለዋል።
ጎን ለጎንም የትራንስፖርት ሥርዓቱን የተሳለጠ ለማድረግ የሚካሄዱ የቁጥጥር ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
የትራንስፖርት ምልልሶችን ማጠናከር፣ የአስፋልት መንገድ ዳር ንግድ እንዳይካሄድ መቆጣጠር፣ በመንገድ ላይ የግንባታ እቃዎች እንዳይቀመጡ የማድረግ ሥራም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
የአዲስ አበባ የትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ አዲስ መመሪያ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
መመሪያው በመዲናዋ በሥራ መግቢያና መውጫ ሠዓት ላይ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ በትራፊክ ግጭት ሳቢያ የሚከተለውን ሕይወት መጥፋት ለመታደግ ብሎም የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ማንኛውም የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪና የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 3፡00 ሰዓትና ከሰዓት በኋላ ከ10፡30 እስከ ምሽቱ 1፡00 ሰዓት ከተማ ውስጥ መግባትም ሆነ በከተማ ውስጥ መንቀሳቀስ፣ ጭነት መጫንም ሆነ ማራገፍ እንዲሁም በዋና ዋና ትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ መቆም የተከለከለ መሆኑን ገልጸዋል።
ያም ሆኖ ገደቡ እሁድና የበዓል ቀናትን እንደማይጨምር አንስተዋል የትራፊክ ፍሰቱን ለማሳለጥ የሚደረጉ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የታክሲ ማኅበራት ተወካዮች በበኩላቸው በየማኅበራቸው የከተማውን ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንደቀድሞ ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይ በዚህ ዓመት ታክሲዎች በትራንስፖርቱን በማይጎዳ መልክ ሰርቪስ እንዲሰጡ መደረጉ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
ማኅበራቱን የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት ቢሮ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።