ኢመደአ ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ከግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርና ከመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ጋር ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፣ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አባተ ምትኩና የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን በቀለ ናቸው።

ስምምነቱ በይነ መረብን ያደረገ የተቀናጀ ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

አሰራሩ ወደ ትግበራ ሲገባ የጡረታ ምዝገባን፣ የጡረታ መዋጮ ክፍያን፣ የጡረታ ተጠቃሚነትንና ሌሎች ስርዓቶችን በማቀናጀትና በቴክኖሎጂ በማዘመን ሥራን እንደሚያቀላጥፍ ተመላክቷል።


 

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በሚፈለገው ጥራትና በተቀመጠቀው የጊዜ ሰሌዳ አሰራሩን ዘርግቶ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጥላሁን በቀለም ፕሮጀክቱ የጡረተኞች ክፍያን የማሰባሰብና ገቢን የማሳደግ ስራን ለማቀላጠፍ የሚያስችል ጥልቅ የአሠራር ለውጥ ለማምጣት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አባተ ምትኩ በበኩላቸው ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓት ፕሮጀክት በመንግስት ትኩረት ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀስ መግለጻቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም