ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):-ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ መደረጉ የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር የተለያዩ ባንኮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ትግበራውን ተከትሎ ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል።
ይህንንም ተከትሎ በቅርቡም የውጭ የሐዋላ ፍሰት የሚስተናገድበት ‘ደቦ’ የተሰኘ የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ መክፈትና ገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ (unite.et) ሥራ ላይ ውሏል።
መተግበሪያው የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ በመክፈት ተንቀሳቃሽ፣የቁጠባና በጊዜ የተገደበ የውጭ ምንዛሬ አማራጭ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ አገራት ዜጎች የውጭ ምንዛሬ ሒሳብ መክፈት የሚያስችላቸው መሆኑ ተጠቁሟል።
ከኢዜአ ቆይታ ያደረጉ የባንክ የሥራ ኃላፊዎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት የማሻሻያ እርምጃን የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በተለይም የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ትልቅ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ እመቤት መለሰ፤በትይዩና በመደበኛ ገበያ የነበረው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተመን ልዩነት ለማክሮ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ ስብራት ነበር ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ የወሰደው ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያ በጥቂት ቀናት ውስጥ በትይዩና በመደበኛ ገበያ ላይ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱም ሐዋላ ላኪዎች ሕጋዊ አሰራርን ተመራጭ በማድረግ የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት አቅም ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
የወጋገን ባንክ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኪዳኔ ገብረ-ስላሴ፤ የ(unite.et) ዲጂታል መተግበሪያ ዜጎች ባሉበት ሥፍራ በመረጡት የኢትዮጵያ ባንክ የውጭ ገንዘብ አገልግሎት የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
የዲጂታል መተገበሪያው የቀረበው አገልግሎትም የሐዋላ ፍሰትን በማሳለጥ የባንኮችን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።
የእናት ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ገነት ሐጎስ፤ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱ ሕጋዊ የሐዋላ አገልግሎትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የ'ደቦ' ሐዋላን ወደአገር ቤት ንቅናቄም ባንኮች በነፃነት በሚሰጡት የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ሒሳብ እንዲከፍቱና ገንዘብ እንዲያስተላልፉ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ክምችትን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
በ‘ደቦ’ የውጭ የሐዋላ ፍሰት አገልግሎት ለሚጠቀሙ ዜጎች ለንግድና ኢንቨስትመንት የሚውል የ100 ቢሊየን ብር ብድር ተዘጋጅቷል።
በዲጂታል መተግበሪያ የሚሰጠው የሐዋላ ፍሰት አገልግሎት ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በአገራቸው የኢኮኖሚ ልማት ቀጥተኛ ተሳታፊ የሚያደርጋቸው መሆኑንም የባንኮቹ የሥራ ኃላፊዎች የገለጹት።
የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓቱን ተከትሎም በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች የሚያቀርቡትን የንግድና ኢንቨስትመንት አገልግሎት ማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያደርጉ ኢትዮጵዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በ (unite.et) ዲጂታል መተግበሪያ የሐዋላ ፍሰት አገልግሎት ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።