ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን አካታች የማንነት ሥርዓትን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):-ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን  አካታች የማንነት ሥርዓትን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ። 

ዓለም አቀፍ የመታወቂያ ቀንን በማስመልከት የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ዛሬ በበይነ መረብ ውይይት ያደርጋል።  

ዓለም አቀፍ የመታወቂያ ቀን መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም ''የመታወቅ መብት'' በሚል መሪ ኃሳብ ይከበራል።

ቀኑ በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር ሲሆን የዚሁ አካል የሆነው የዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የቪዲዮ ውይይት ዛሬ ይካሄዳል ተብሏል። 

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቤኔዘር ፈለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን ግለሰብና ማኅበረሰብን የሚያበቃ አካታች የማንነት ሥርዓትን አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል።

የቀኑ መከበር ማንነትን መያዝ ሰብዓዊ መብት ብቻ ሳይሆን የትኛውንም አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለዜጎች ለማስገንዘብ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቀኑን በማስመልከት ዛሬ ከቀኑ ከ11 ሰዓት ጀምሮ በከፍተኛ የዘርፉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የቪዲዮ ኮንፈረንስ ማዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የቪዲዮ ኮንፈረንሱ ዋና ዓላማ ዲጂታል መታወቂያ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችና የዘርፉ መሰረተ ልማቶች ላይ ትኩረት በማድረግ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አማካሪ ጆቴወርቅ አየለ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ኃሳባቸውን ያጋራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዓለም አቀፍ የመታወቂያ ቀን በየዓመቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን ቀኑ የተረጋገጠ የማንነት መገለጫ ያለውን መሰረታዊ ጠቀሜታና ማንነት ሁሉን አካታች ሊሆን እንደሚገባ ማስገንዘብን ዓላማ ያደረገ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም