ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን የተመለከተ የፓናል ውይይት ዛሬ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን የተመለከተ የፓናል ውይይት ዛሬ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):- የ2024 ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን (International Identity Day) የተመለከተ የፓናል ውይይት ዛሬ ይካሄዳል።
በበይነ መረብ በሚካሄደው የከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት በዲጂታላይዜሽን የአስተዳደር ስርዓትን ማሻሻል ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ አማካሪ ጆቴወርቅ አየለ ንግግር ያደርጋሉ።
የዲጂታል ማንነት ላይ የሚሰራው የፓን አፍሪካ ተቋም ‘አይዲ 4 አፍሪካ’ ዋና ሊቀ መንበር ዶክተር ጆሴፍ አቲክ፣ የዓለም ባንክ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ጁሊያ ክላርክና የዩጋንዳ ብሔራዊ የማንነት ማረጋገጫና ምዝገባ ባለስልጣን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ጆሴፍ ቢርቦንዋ በፓናል ውይይቱ ላይ ተጋብዘው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዓለም አቀፍ የመታወቅ ቀን በየዓመቱ እ.አ.አ መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን ቀኑ የተረጋገጠ የማንነት መግለጫ ያለውን መሰረታዊ ጠቀሜታና ማንነት ሁሉን አካታች ሊሆን እንደሚገባ ማስገንዘብን አላማ ያደረገ ነው።
በዓሉ የሚከበርበት 16 ቀን የተመረጠው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግብ ተራ ቁጥር 16 ከተቀመጠው የማንነት ባለቤትነት ራዕይ ጋር በማስተሳሰር ነው።
በግቡ ላይ እ.አ.አ በ2030 ሁሉም የዓለም ነዋሪ የልደት ምዝገባን ጨምሮ ሕጋዊ ማንነት ማግኘት እንዳለበት ተቀምጧል።