ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በሻይ ልማት ዘርፍ በትብብር መስራት ትፈልጋለች - አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር በሻይ ልማት ዘርፍ በትብብር መስራት እንደትምትሻ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ገለጹ።

በኢትዮጵያ በሻይ ኢንዱስትሪ ከተሰማሩ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት የተወጣጣ የልዑካን ቡድን በኬንያ የሻይ ምርትና ኢንዱስትሪ ተሞክሮ መቅሰምን አላማ ያደረገ ጉብኝት አድርገዋል።


 

ልዑካን ቡድኑ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ያቀፈ መሆኑም ተገልጿል።

ቡድኑ ከኬንያ የሻይ ልማት ኤጀንሲ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በኬንያ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችና የሻይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከእርሻ እስከ ሽያጭ ባለው ሂደት ያላቸውን ትስስር አስመልክቶ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ልዑካን ቡድኑ የሻይ ቅጠል እርሻ፣ ማቀነባበሪያ ፋብሪካና የማምረቻ ማሽኖችን ጎብኝቷል።

ጉብኝቱ ኢትዮጵያና ኬንያ በሻይ ልማት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንዲሁም አገራቱ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጎለብት ተገልጿል።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ የኬንያ የሻይ ልማት ኤጀንሲ በሻይ ምርትና ኢንቨስትመንት ያለውን ተሞክሮ በማጋራቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያና ኬንያ የሻይ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ልምድ በመለዋወጥ የዜጎቻቸውን ኑሮ ማሻሻል እንደሚችሉ መግለጻቸውን ኢዜአ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም