ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቢሾፍቱ ከተማን የኮሪደር ልማት ስራ ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቢሾፍቱ ከተማን የኮሪደር ልማት ስራ ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017(ኢዜአ):- የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቢሾፍቱ ከተማን የኮሪደር ልማት ስራ ጎብኝተዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሰጡትን የስራ መመሪያ በመቀበል በቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት ስራ ያለበትን ደረጃ መጎብኘታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ከከተማው አመራሮች፣ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሀደ ስንቄዎች እንዲሁም ከነዋሪ ተወካዮች ጋር በተያዙ እቅዶችና በቅንጅት በሚሰራበት አግባብ ላይ ውይይት መደረጉንም አመልክተዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በአምስት አካባቢዎች በሰፋፊ ቦታ ላይ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በውስጡም የመንገድ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ የሕዝብ መዝናኛ ፓርክ እንዲሁም መንገዶችን የማስዋብ ስራዎች መካተታቸውን ገልጸዋል።
ቢሾፍቱ በተፈጥሮ የታደለች ከሰባት ሀይቆች በላይ ያላት የቱሪስት መዳረሻ ከተማ መሆኗን ጠቁመው የኮሪደር ልማት ስራው ሲጠናቀቅ ይበልጥ የቱሪስት መስህብነቷን እንደሚጨምርና የከተማዋን የወደፊት እድል ከፍ የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።