ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትሰራለች- አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ትሰራለች- አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 3/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደምትሰራ በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ገለጹ።
አምባሳደር ገነት የሹመት ደብዳቤያቸውን ቅጂ ለሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ አገራት ልዩ አማካሪ ሚካኤል ቦግዳኖቭ አቅርበዋል።
አምባሳደሩ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተላከ ሰላምታና የመልካም ምኞት መልዕክት እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ለሚኒስትር ዴኤታው የተላከ ሰላምታ አድርሰዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ገነት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ አበክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚካኤል ቦግዳኖቭ ሩሲያ አምባሳደር ገነት የሁለቱን ወዳጅ አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት ለሚያደርጉት ጥረት አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንደምታደርግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያና ሩሲያ 126 ዓመታት የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ኢዜአ ሞስኮው ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።