በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "የጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ" ንቅናቄ አካል የሆነ የአረንጓዴ ልማት እየተከናወነ ነው

መስከረም 3/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል "የጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ" ንቅናቄ አካል የሆነ የአረንጓዴ ልማት ተግባራት ከተቋማትና ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ገለጸ ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከተሞችን ጽዱ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው።

በአገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው" የጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ" ንቅናቄ በክልሉ ተግባራዊ መድረጉን በመቀጠል ከተለያዩ ተቋማትና ባለሃብቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በተለያዩ የክልሉ ከተሞች 248 የአረንጓዴ ልማት ቦታዎችን ለማልማት ተቋማትና ባለሃብቶች ቦታዎችን ተረክበው እያለሙ መሆኑን አስረድተዋል።

በአረንጓዴ ልማት ስራው የክልል መንግስት ተቋማት ባሉባቸው ከተሞች በተጨማሪ በዞን፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮችም ስራውን ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ከአረንጓዴ ልማት ስራው ጎን ለጎን በ10 የክልሉ ከተሞች በ200 ካሬ ላይ የሚያርፉና በዘመናዊ መልክ የሚገነቡ መጸዳጃ ቤቶች የንቅናቄው አካል እንደሆኑም ጠቁመዋል።

እነዚህ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች በተያዘው ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑም አክለዋል።

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር በሰጣቸው ቦታ የአረንጓዴ ልማት ስራ እያከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር አተረፈ ታምራት ናቸው።


 

ተቋማቸው የተከላቸው ችግኞች ጸድቀው ከተማዋን ውብና ጽዱ እንዲሆኑ እየተንከባከበ ነው ብለዋል።

የቡታጅራ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ወልዩ ከበደ በበኩላቸው፤"የጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ" ንቅናቄ አካል የሆነ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤት ከዘጠኝ ሚሊዮን በሚበልጥ ወጪ እየተገነባ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

የመጸዳጃ ቤቱን ግንባታ በሶስት ወራት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን፤ ዲዛይኑም ለአካል ጉዳተኞና አቅመ ደካሞች ምቹ የሆነና የአረንጓዴ ልማት ስራ የሚከናወንበት ነው ብለዋል።

በከተማው 22 ባለሃብቶች፣ 5 የክልል ተቋማትና የሃይማኖ ተቋማት የአረንጓዴ ልማት ስራውን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡታጅራ ነዋሪ አቶ ወንድወሰን ሃይሌ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማው በህብረተሰቡ ተሳትፎ እተከናወነ ያለው የአረንጓዴ ልማት ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በከተማው ካለው ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ እጽዋቶችን በመንከባከብ የቆየ ልምድ እንዳላቸው አመልክተው፤ ከከተማው አስተዳደር የተሰጣቸውን ቦታውን የበለጠ ለማስዋብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም