በቡና የወጪ ንግድ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ - ኢዜአ አማርኛ
በቡና የወጪ ንግድ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ተገኘ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም በቡና የወጪ ንግድ ከ196 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ በማግኘት በታሪክ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት መቻሉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።
ገቢው የተገኘው ወደ ውጭ ሀገራት ከተላከ 42 ሺህ 322 ቶን ቡና መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ(ዶ/ር) ገልጸዋል።
የተገኘው ገቢ እስከዛሬ ከነበሩ ወራቶች ክብረ ወሰን የሰበረ ሆኖ መመዝገቡን አመልክተዋል።
ገቢው ከታቀደው አንጻር በመጠን 165 በመቶ እንዲሁም ከገቢ አንጻር የ143 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
የ2016 ዓ.ም የሐምሌና ነሐሴ ወራት የሁለት ወራት አፈጻጸም በድምሩ በመጠን 82 ሺህ 853 ቶን ቡና በመላክ 377 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።
ይህም በ2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ሁለት ወራት ከነበረው አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በመጠን 32 ሺህ 925 ቶን(66 በመቶ) እንዲሁም በገቢ 110 ሚሊዮን(41 በመቶ) ጭማሪ የታየበት መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።