ኢትዮጵያ የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ሁለት ተደለደለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2025 በሚካሄደው 24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ተጋጣሚዎቿን አውቃለች።

የማጣሪያ ውድድሩ በታንዛንያ አዘጋጅነት ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በታንዛንያ ይካሄዳል።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የማጣሪያ ድልድል ዛሬ በዳሬ ሰላም ይፋ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።

24ኛው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ በስድስት ዞኖች ተከፍሎ እንደሚካሄድና 48 ሀገራት እንደሚሳተፉበት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) አስታውቋል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም