የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታዎችን ባህላዊ እሴቶች በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታዎችን ባህላዊ እሴቶች በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች የሽኖዬ እና ጎቤ ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ተዘዋውረው እያቀረቡ ይገኛሉ።

የዚህ ቱባ ባህላዊ ሁነት ይዘት ጭጋጋማው የክረምት ወራት አልፎ የፀደይ ወቅት ሲገባ የሚከወን የልጃገረዶችና የወጣት ወንዶች ባህላዊ ጨዋታ ነው።

የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የሚከወን ሲሆን ወጣቶች በየቤቱ እና በየጎዳናው በመዘዋወር አንድ ላይ በመሰባሰብ የሚያከብሩት ነው።


 

በዛሬ ዕለትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ጨዋታውን በማቅረብ እንኳን አደረሷችሁ ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር፣ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳውና ሌሎችም ተገኝተዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእከትም አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የእድገት፣ የአንድነትና የእርቅ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

የጎቤና ሽኖዬ ጨዋታዎችን ባህላዊ እሴት በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህሎችን መጠበቅ፣ መንከባከብና ማሳደግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የጎቤና ሽኖዬ ባህላዊ እሴቶችን ጨምሮ ሌሎችም ለኢትዮጵያዊያን አብሮነትና ጥብቅ የባህል ቁርኝት የላቀ ተርጉም እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በመሆኑም በተለይም ወጣቶች ቱባ ባህሉን ጠብቀው ለማቆየት እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀው በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም