የጤና ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነትን ለማሻሻል በትኩረት ይሰራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 በጀት ዓመት በሐረሪ ክልል የጤና ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥና ተደራሽነት ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ የበጀት ዓመቱን የትኩረት አቅጣጫዎች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በሽታን መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የማህበረሰብ ፍላጎት መነሻ ያደረገ መሠረታዊ የመድኃኒትና የሕክምና ግብአቶች አቅርቦት ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡን ውጤታማነት ለማሻሻል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የተቋማቱን ባለሙያዎች የሙያ ስነ ምግባርና የመፈፀም አቅም በማሳደግ ተቋማቱን በበቂ የሰው ኃይል ማደራጀት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ ነው ያሉት ኃላፊ።
በክልሉ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከልና መቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የወባና ኮሌራ በሽታዎች የመከላከል ስራ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እንደሚጠቀሱ አመልክተዋል።
ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የዝግጁነትና የምላሽ ስርዓትን ማዘመንና የማጠናከር ስራዎች እንደሚከናወንም ገልጸዋል።
የእናቶች፣ ሕጻናትና የወጣቶች ጤና እንዲሁም ስርዓተ ምግብን ማሻሻል የበጀት ዓመቱ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን በመጠቆም።
የማህበረሰብ ግንዛቤ ፈጠራ፣ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋትና የጥራት ደረጃን በማሳደግ የክልሉን የጤና ቱሪዝም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በመገንባት ላይ የሚገኙ የጤና ተቋማትን በበጀት ዓመቱ በማጠናቀቅ ወደ ስራ እንዲገባ ይሰራል ማላታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።