በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ ባለሙያዎችን ማፍራት ተችሏል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉን የፕሮጀክቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ገለጹ፡፡
የታላቁ አባይ ወንዝ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ከምድሯ የሚፈሰውን ውሃ ለዘመናት ሳትጠቀምበት እልፍ ዓመታት ነጉደዋል።
ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ግን በዜጎች ገንዘብና ጉልበት ግድብ ሰርቶ ከወንዙ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የግንባታ መሰረት መቀመጡ ይታወሳል።
ለዚህም ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን ያለምንም ስስት ለግንባታው አስተዋጽኦ ያደረጉ ሲሆን በርካቶችም የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን በመገባደድ ላይ ያለው በዜጎች እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት ነው፡፡
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ እስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን፤ ለፕሮጀክቱ ስኬት ከዲዛይን ጀምሮ አስከ ግንባታው የኢትዮጵያውያን ሚና የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር በአንድ ጊዜ እስከ 15 ሺህ ዜጎች በግንባታው ሂደት ላይ በተለያዩ ሙያዎች ይሳተፉ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በግንባታው ሌት ከቀን በመትጋት በስኬት መንገድ ዘልቀው ለግድቡ እውን መሆን ዘላለማዊ አሻራቸውን በማሳረፍ የሚያኮራ ተግባር ፈፅመዋል ብለዋል።
በግንባታው የረጅም ዓመት ልምድ በቀን ሰራተኝነት የጀመሩ በርካታ ወጣቶች አሁን ላይ ከፎርማን እስከ ሱፐርቫይዘርነት መድረሳቸውን ገልጸዋል።
በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራት ስለመቻሉም አንስተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 13 ተርባይኖች እንዳሉት ገልጸው፤ የጀነሬተር አካል እስከ 12 ሜትር ዲያሜትርና ከ460 ቶን በላይ ክብደት ስላለው በትራንስፖርት አጓጉዞ ለማድረስ ፈታኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ነገር ግን በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው አቅማቸውን በማጎልበት ዛሬ ላይ ግብዓቶችን በማምጣት ከዚሁ እንዲገጣጠሙ ማድረግ የሚችሉበት አቅም ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ ኢትዮጵያ ለምትገነባቸው የሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክቶች የሙያ ብቃትና ዝግጁነት እንዲኖር አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
የኬ.ቲ ኢንዱስትሪያል ሶሉሽን ሥራ አስኪያጅ ሞላ አስማረ፤ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በሂደት የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው የተርባይን ማቀዥቀዝ ክፍል ዋነኛው ክፍል የሆነውን ራዲያተር በራሳቸው መስራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አብዛኛውን የፕሮጀክቱን ግብአት በራሳቸው መሥራት እንደሚችሉ ገልጸው፤ ከአቅም ግንባታ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ያስችላልም ብለዋል፡፡
በህዳሴው ግድብ ላይ በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሳተፉ በርካታ ወጣቶች በየዘርፉ የኤክስፐርት ደረጃ ላይ የደረሱ እንዳሉም አስታውሰዋል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ በቀን ሥራ ይሳተፉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች እውቅትንና ክህሎታቸውን በማዳበር ከፍተኛ የሙያ ብቃት ላይ መድረሳቸውንም ገልጸዋል።
በብየዳ ሥራ የተሰማሩት ወጣት ያየህ የሻንበል እና ህይወት አስማረ፣ በግንበኛ ሙያ የተሰማራችው ወጣት ደጌ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በማንኛውም ቦታ በብቃት መሥራት የሚያስችል አቅም መፍጠር ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።