ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ መጠን ስርጭት እየቀነሰ ይሄዳል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት 10 ቀናት በሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የዝናብ መጠን ስርጭት እየቀነሰ ሲሄድ በሌሎች ቦታዎች  መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል የዝናብ መጠኑ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል አመላክቷል።

የኢትየቶጵያ ደቡባዊው ክፍል ሁለተኛውን የዝናብ ወቅት ቀስ በቀስ ማግኘት እንደሚጀምሩም ጠቁሟል።

የሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ እንዲሁም መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይመዘገባል ሲልም ነው የተነበየው።

በፀሀይ ሀይል የሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ሊያስከትሉ እንደሚችሉም የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በትግራይ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከቀላል እስከ ከባድ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአንፃሩ አፋር፣ ኦሮሚያ  ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች፣ አማራ ክልል ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ጋንቤላ ክልል፣ ትግራይ ክልል ደቡብና ደቡብ ምስራው ዞኖች ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሱማሌ እና ሀረሪና ክልሎች እንዲሁም ድሬዳዋ ከፍ ያለ ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

በአብዛኞቹ የመኸር ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖራቸውም ይጠበቃል።

በመሆኑም በማፍራት ላይ ላሉ፤ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች እንዲሁም ለአትክልትና ፍራፍሬዎች የላቀ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ከአዋሽ ተፋሰስ የቆቃ፣ ተንዳሆና ከሰም ግድቦች፤ ከዓባይ ተፋሰስ ጣና በለስ፣ ርብና ፊንጫ ግድቦች፤ ከውሀ  ብዛት ጋር በተያያዘ በታችኛው የተፋሰሱ አካባቢዎች ጫና እንዳያሳድሩ ክትትል ማድረግ ይገባል ሲል አሳስቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም