የልማት ስራዎች የሁሉንም ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የልማት ስራዎች የሁሉንም ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2017(ኢዜአ):- የልማት ስራዎች የሁሉንም ተሳትፎና ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባዋን ጨምሮ ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በመዲናዋ 21ኛው የምገባ ማእከል በይፋ ስራ አስጀምረዋል።
የምገባ ማእከሉ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ አየር ጤና አካባቢ በበረከት ወርቁ (በበረከት ገበሬዋ) ድጋፍ የተገነባ ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአዲስ አበባ የተገነቡ የምገባ ማእከላት በቀን አንድ ጊዜ በራሳቸው መመገብ የማይችሉ ወገኖችን የሚመግቡ ናቸው ብለዋል።
ለማእከላቱ እውን መሆንም የተለያዩ የግል ተቋማትና ባለሃብቶች እያደረጉት ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የምገባ ማዕከላቱ ወገኖችን ከመመገብም ባለፈ ለብዙዎች የስራ እድል እየፈጠሩ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
ከበረከት ወርቁ ጋር በመተባበር አየር ጤና አካባቢ የተገነባው 21ኛው የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከልም በዛሬው እለት ለአገልግሎት በቅቷል ብለዋል።
የማእከሉን ግንባታ አጠናቀው ያስረከበችው ባለሃብቷ በረከት ወረቁ፤ ለዜጎች የሚጠቅም በጎ ተግባር መፈፀም ከምንም በላይ የላቀ ደስታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች።
የተገነባው የምገባ ማዕከል በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የግብርና ምርቶች የሚሸጡበት ሱቆች የተካተቱበት ስለመሆኑ ጠቅሳለች።
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር በቀጣይም 22ኛውን የተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከል ለመገንባት ዝግጁ መሆኗን ባለሃብቷ አረጋግጣለች።