ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በሚኖሩባቸው አገራት አከበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በሚኖሩባቸው አገራት አከበሩ
አዲስ አበባ፤መስከረም 1/2017 (ኢዜአ):- በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የአዲስ ዓመት በዓልን አክብረዋል።
በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዲስ ዓመትን ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት አመራሮች እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን ኬንያ ያደረጉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ በተገኙበት ተከብሯል።
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ የኢትዮጵያ አዲስ አመት እንደ አገር አንድነታችን የምንጠናክርበትና የወደፊት የጋራ እድሎቻችንን በጋራ የምንቀበልበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።
የዘንድሮውን አዲስ ዓመት ስናከብር ኢትዮጵያና ኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበት 60ኛውን ዓመት ጭምር በማክበር እንደሆነ ገልጸዋል።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዴኒስ ምቡሩ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል።
በሕንድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቷ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን አዲስ ዓመትን አክብሯል።
የኤምባሲው ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ብዙነሽ መሰረት ኢትዮጵያ የ13 ወራት የዘመን አቆጣጠር ያላት አገር መሆኗንና ይህም በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በጋራ እንዲያከብሩ የሚያደርግ ልዩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በተለያዩ መስኮች ስኬት ማስመዘገቧንና ይህንንም በአዲሱ ዓመት ዘላቂ ልማትን እውን በማድረግ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሕንድ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እንደምትሰራም ገልጸዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ ኢትዮጵያውያን፣ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ ዓመት በዓል በጣልያን ሮም ተከብሯል።
በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ አዲሱ አመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና የምንበለጽግበት ጊዜ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አዲሱ ዓመት የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ ተግተን የምንሰራበት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልማትን ለማረጋገጥ ጠንካራ ርብርብ የሚደረግበትና በጋራ የምንቆምበት ዓመት ነው ብለዋል::
የዳያስፖራ ተወካዮችም በበኩላቸው ኤምባሲው ዳያስፖራው ከአገሩ ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጠናከር እያከናወነ ያለውን ስራ አመስግነው በአዲሱ ዓመት ለተሻለ ውጤት እንደሚተጉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የ2017 አዲስ ዓመት አንካራ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተከብሯል።
በተርኪዬ የኢትዮጵያ አምባሳደር አደም መሐመድ አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ እና የስኬት ዘመን እንዲሆን ተመኝተዋል።
የኤምባሲው ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ልማት፣ሰላምና ዲሞክራሲ ግንባታ ስራ የበለጠ አስተዋጽኦ በሚያበረክት መልኩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በተቀናጀና በላቀ ሁኔታ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።
ጀርመን፣ኩዌትና ዩናይትድ ኪንግደም በዓሉ ከተከበረባቸው አገራት መካከል ይገኙበታል።