ቀጥታ፡

የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2017(ኢዜአ):- ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች አዲሱን ዓመት በማስመልከት ለኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሼን ኪንሚን ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና የራሳቸው የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ባህልና ታሪክ ያላት ድንቅ ሀገር ናት ያሉት ሼን ቻይና ለዚህ ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።


 

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ተመኝተው ኢትዮጵያ የተዋበች ብዝሃ ሀገር ናት፤ ብዝሃ ማንነቶች ለኢትዮጵያ አንድነት ድምቀት ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የተፈጥሮ ሀብትና የሰለጠነ የሰው ኃይል በመጠቀም ስኬት ማስመዘገብና ኢትዮጵያም የአፍሪካ መሪ መሆን እንደምትችል ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አል-ራሺዲ ለኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመትን ተመኝተዋል።

በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲም አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የብልፅግና የስኬት እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያውያን አዲሱ ዓመት የሰላምና የደስታ እንዲሆን መልዕክቱን አስተላልፏል።

በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ሬዛይ ለኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።


 

በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አንድሪው ኦኪንደን በኢትዮጵያ ያለፈው ዓመት በርካታ መልካም ነገሮች የነበሩት ጊዜ ነው ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመውሰድ ያሳየውን ቁርጠኝነት እንደምታደንቅ ገልጸው ማሻሻያው ለኢትዮጵያውያን ብልጽግናና የስራ እድልን እንደሚያመጣ አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሀገራቸውን ጨምሮ የዓለም አቀፍ አጋሮችን ንግድና ኢንቨስትመንት እንደሚስብ ተናግረዋል።

በአዲሱ ዓመትም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ ሰላም የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶክተር አቭረሃም ንጉሴ ኢትዮጵያውያን እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ብለዋል በመልካም ምኞች መልዕክታቸው።

2017 የሰላም፣ የብልፅግና የፍቅር ዓመት እንዲሆንም አምባሳደሩ ተመኝተዋል።


 

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን ይዞ እንዲመጣ እመኛለሁ ብለዋል።

አዲስ የተሾሙት አምባሳደር በቆይታቸው የኢትዮጵያንና የፈረንሳይን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።


 

በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞት ተመኝተዋል።

ሕንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ኦስትሪያ፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ሞሮኮና ሜክሲኮ በኤምባሲዎቻቸው በኩል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም