ቀጥታ፡

በክልሉ ለመጪው ጊዜ ተስፋ የሆኑ ተግባራት ተከናውነዋል- ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ

ባህር ዳር፤ ጳጉሜ 5/2016  (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በችግር ውስጥ ቢታለፍም ለመጪው ጊዜ ተስፋ የሆኑ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።

የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት መግቢያ ዋዜማ "አዲስ ዓመት፣ አዲስ እይታና አዲስ መገለጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ በስነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የ2016 ዓ.ም በክልሉ ችግሮች ያጋጠሙበት ቢሆንም በዚያ ውስጥም በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል።

በክልሉ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከተደረጉ ጥረቶች ጎን ለጎን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ልማቶች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም አብሮነትን የሚያሳድጉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ለአዲሱ በጀት ዓመትና ለመጪው ጊዜ አሻጋሪና ተስፋ የሆኑ ስራዎች በቅንጅት ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

አዲሱ ዓመትም ባለፈው ዓመት በተከሰቱ ችግሮች ያጋጠሙ መጥፎና እኩይ ተግባራት ተወግደው "የደስታ፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የተስፋ ዓመት እንዲሆን ከህዝባችን ጋር በጋር የምንሰራበት ነው" ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ አዲሱ ዓመት የተስፋ፣ የፍቅርና የሰላም እንዲሆን በመመኘት ለመላው የአማራና የኢትዮጵያ ህዝብ "እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ" የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋየ በበኩላቸው፤ "የአገራችን የአዲስ ዓመት በዓል የአባቶቻችን የስነ ፈለግ፣ የሂሳብ ቀመርና ጥበብ ውጤት ነው" ብለዋል።

በዚህም የዘንድሮው አዲስ ዓመት የበረከትና ጥጋብ ዓመት እንዲሆን የምንተጋበት ዓመትመሆኑን ገልጸዋል።

"አዲስ ዓመት፣ አዲስ እይታና አዲስ መገለጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ከተማ እየተከበረ ባለው የበዓል ዋዜማ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ባልድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም