በአዲሱ አመት እስከ አሁን በሰራነው ሳንረካ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሕዝባችንን ዝቅ ብለን እናገለግላለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ አመት እስከ አሁን በሰራነው ሳንረካ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሕዝባችንን ዝቅ ብለን እናገለግላለን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 4/2016(ኢዜአ)፦ በአዲሱ አመት እስከ አሁን በሰራነው ሳንረካ ይልቁንም የዛሬውን ትውልድ ከነገው ትውልድ ጋር በማስተሳሰር የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሕዝባችንን ዝቅ ብለን እናገለግላለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች ኤቤቤ ለ2017 ዓም የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ከንቲባዋ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክትም በሀገር ውስጥና በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፤ እንኳን ለ2017 ዓ.ም በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ብለዋል።
አዲሱን አመት የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የስኬት ያድርግልን ሲሉም አክለዋል ከንቲባዋ፡፡
ባሳለፍነው ዓመት እንደ ሀገር የተጋረጡብንን በርካታ ፈተናዎች በድል የተሻገርንበት፣ ስኬታማ ስራዎችን በመስራት ውጤቶችን ያስመዘገብንበት፤ እና የሕዝባችንን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ያደርግናቸው ጥረቶች ፍሬ ማፍራት የጀመሩበት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መልክ የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባም በፍቅር የደመቀች እና በህብረ-ብሔራዊነት ያጌጠች ከተማ መሆኗን በተግባር እያሳየች የአብሮነት፣ የመተባበርና የመከባበር እሴትን አጠናክራ ያሳየችበት አመት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ባሳለፍነው አመት አብሮነታችንን በማጠናከርና የበጎ ተግባር ስራዎቻችንን በማስፋት፡ የበርካታ የከተማችንን አቅመ ደካማ፣ የሀገር ባለውለታዎች እና ለችግር የተጋለጡ ወገኖችቻንን እንባ ያበስንበት፣ ትኩረትና ክብር ተነፍጓቸው የኖሩ ወገኖቻችንን ዝቅ ብለን በማገልገል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ያጎላንበት አመትም ነውም ብለዋል፡፡
ልማታችን ማንንም ወደ ኋላ የተወ አይደለም ሲሉም አክለዋል ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው፡፡
በመሆኑም ባሳለፍነው ዓመት እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸው የተሻሉ ውጤቶችን በመዘከር በቀጣይ ትልሞቻችን ላይ የሰላምና የልማት ሀይሎችን በማስተባበር በርካታ ሀገር አሻጋሪ ተግባራትን ለማከናወን ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡
በአዲሱ አመት እስከ አሁን በሰራነው ሳንረካ ይልቁንም የዛሬውን ትውልድ ከነገው ትውልድ ጋር በማስተሳሰር የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በብዙ ጥረት፣ በብዙ ትጋትና በማያቋርጥ ልፋት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመስራት ሕዝባችንን ዝቅ ብለን እናገለግላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ዓመት በአንድነት የምንነሳበት፤ ከማይረቡን አጀንዳዎች ርቀን፡ እጆቻችንን ለስራ በማትጋት የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በማረጋገት ሰላማችንን የምናፀናበት ከውጭና ከውስጥ የሚተናኰሉንን ሀይሎች በመመከት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አስጠብቀን የምንቀጥልበትና የነዋሪዎቻችንን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ተግተን የምንሰራበት ፍሬያማ ዓመት እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ ብለዋል፡፡