በአዲስ አበባ የዛሬ የዋዜማ የገበያ ውሎ ምን ይመስላል? - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የዛሬ የዋዜማ የገበያ ውሎ ምን ይመስላል?

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ ኢዜአ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ተዘዋውሮ የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የቁም እንስሳና የሌሎች ግብይቶችን ተመልክቷል።
በሸጎሌ ገበያ ሲገበያዩ ያገኘናቸው አቶ ወንድወሰን ከበደ ከባለፈው የፋሲካ በዓል ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮ ገበያ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
በተለይም ቀደም ባለው የበዓል ገበያ የበግ ዋጋ ከ10 አስከ 11 ሺህ ብር ይገዛ እንደነበር ገልፀው አሁን ላይ 16 እና 17 ሺህ መድረሱ ይናገራሉ።
የቁም ከብት በብዛት መግባቱን ገልፀው ዋጋቸው ከ40 እስከ 200 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በዛው በሸጎሌ ገበያ ያገኘናቸው አቶ ጥላሁን በርሄ ናቸው።
አቶ ጥላሁን በዘንድሮው የአዲስ ዓመት ገበያ መጠነኛ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ እንደሌለ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በመገናኛ ሾላ ገበያ ያገኘናቸው አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በዘንድሮው የአዲስ ዓመት በዓል የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩ ይናገራሉ።
የሸኖ፣ የጎጃምና የወለጋ አንድ ኪሎ ቅቤ ቂቤ መያዛቸው ገልፀው ከ750 እስከ 900 ብር ድረስ፤ ቆጮ ከ200-250 ብር፤ በተመሳሳይ ማር ከ500 እስከ 700 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ነግረውናል።
ከሌሎች ምርቶች በተለየ ሁኔታ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ ምርቶች መካከል ኮረሪማ እንደሚገኝበትም ለማወቅ ችለናል።
በአዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው ሾላ ገበያ ያገኘናቸው ወይዘሮ አልማዝ ገመዳ የዶሮ ዋጋ ከባለፈው የፋሲካ በአል ሲነፃፀር የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ገልጸዋል።
እንቁላል ከ12 ብር ጀምሮ እስከ 18 ብር ድረስ እየተሸጠ እንደሚገኝም ተዘዋውረን ተመልክተናል።
ሸማቾቹ ነጋዴው ማኅበረሰብ የወቅቱ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶች ሊያቀርቡ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነው መተጋገዝና መተባበራችን በማስቀጠል ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተጋገዝ በደስታ ልናሳልፈው ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።