የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ2017 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ2017 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ2017 አዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡
የአገልግሎቱ የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በጉጉት ይጠብቃሉ፤ ጋራ ሸንተረሩም የዚህ አዲስ ዓመት ጠባቂ ይመስል ኩልል ባለ ንጹሕ የምንጭ ውኃ ፏፏቴ፣ በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት አበቦች ይዋባሉ፡፡ አዲስ ዓመታችን ዐዳዲስ ዕቅዶችን መተግበር የምንጀምርበት፣ ተነፋፍቀው የከረሙ ተማሪዎችና መምህራን በጉጉት የሚገናኙበት፣ በመኸር የተዘራው የሚያሸትበት፣ ዐዲስ ተስፋና ጉጉት የሚፈነጥቅበት ነው፤ ለዚህም ነው በላቀ ጉጉት የሚጠበቀው፡፡
የተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም በፈተናዎች ውስጥ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግበንበታል፡፡ ለዘመናት ለመነጋገር ነውር የነበረውን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በአጀንዳነት አንሥተን መሻታችን እንዲሳካ መንገድ ከፍተናል፡፡
ከዘርፈ ብዙ ትብብር አንጻር የብሪክስ አባልነትን ጠይቀን አሳክተንበታል፡፡ የሕዳሴ ግድባችንን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ አድርሰን ተጨማሪ ተርባይኖች ታዳሽ ኃይል እንዲያመነጩ አስችለንበታል፡፡
በጀመርናቸው የግብርና ዘርፍና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄያችን ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አሸንፈንበታል፡፡
በሀገር ውስጥ የነበሩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን በሀገር በቀል እሴቶቻችንና አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ተከትልን፣ ከዚያ አለፍ ያሉትን ደግሞ በሕዝባችን ትብብርና የፀጥታ ኃይላችን ትጋት በተሰራው ሕግ የማስከበር ሥራ ፀረ-ሕዝብ ታጣቂ ሃይሎች ለሀገር ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ኅብረተሰቡ ወደ ቀየው ተመልሶ ወደ መደበኛ ሕይወት ገብቷል፡፡ በግጭቶች ውስጥ ይሳተፉ ከነበሩ ኃይሎችም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ ጥሪን ተቀብለው፣ የተሐድሶ ሥልጠና እግኝተው በቁጭት ሕዝባቸውን ለመካስ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል፡በጀመርነው ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ደግሞ ወደ ዘላቂና አወንታዊ ሰላም በዐዲሱ ዓመት እንደምንገባ ተስፋ ሰንቀናል፡፡
2016 ዓ/ም የግብርና ሥራችን ከዝናብ ወቅት በተጨማሪ በበጋ መስኖ የላቀ ስኬት ያስመዘገበበት ዓመትም ነበር፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ የተከልናቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች በከፍተኛ ደረጃ ምርት መስጠት የጀመሩበት፤ ዘንድሮም የራሳችንን ክብረ ወሰን አሻሽለን በአንድ ጀምበር ከ615 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የተከልንበትና በለውጡ ዓመት በአጠቃላይ ከ40 ቢሊዮን ችግኞች በላይ ያደረስንበት ዓመት ነበር፡፡
በሌማት ትሩፋት ንቅናቄያችን የጓሮ አትክልትና እንስሳት ርባታ ላይ በማተኮር መሠረታዊ ለውጥ አምጥተንበታል፡፡ በዚህም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የሥነ ምግብ ሁኔታችንን ማሻሻል ችለናል፡፡
በዚህ በተጠናቀቀው ዓመት በኢንዱስትሪ ዘርፉም ስኬት አስመዝግበናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ተከፍተዋል፡፡ የተኪ ምርትና የኢትዮጵያን ይሸምቱ ንቅናቄዎችም ፍሬያማ ነበሩ፡፡
የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት የመላክ ጅምሮች ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይተውናል፡፡ በዲጂታል ዘርፉ ትልቅ ዐልመን ትልቅ ንቅናቄ ውስጥ ገብተናል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “ኮደሮችን” ሥልጠና አስጀምረናል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በተሟላ መልኩ መተግበር ጀምረንበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ አስገብተን የቱሪዝም ዘርፋችንን ተጨማሪ እሴት አጎናጽፈንበታል፡፡
በአጠቃላይ 2016 ዓ.ም በበርካታ ስኬቶች ያጠናቀቅነው ዓመት ሆኗል፡፡ በመጪው አዲስ ዓመት ደግሞ በተሻለ መሠረት ላይ ቆመን የላቀ አፈጻጸምና ስኬት ለማስመዝገብ የጠሩ ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ በዚህ ላይ የመላው ሕዝባችን ተስፋና ርብርብ ሲታከልበት አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የብልጽግና ዘመን እንዲሆን እንመኛለን፡፡
በድጋሜ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ!