ቀጥታ፡

በክልሉ ጠንካራ የፓርቲ አደረጃጀት መፍጠር የሚያስችሉ ተቋማትን የመገንባት ሥራ እየተሰራ ነው - አቶ አብርሀም ማርሻሎ 

ሀዋሳ ፤ጳጉሜን 05/2016 (ኢዜአ)፦ ሲዳማ በክልል ጠንካራ የፓርቲ አደረጃጀት መፍጠር የሚያስችሉ ተቋማትን የመገንባት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ በብልፅግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ገለፁ ።

በሀዋሳ ከተማ አራት ክፍለ ከተሞች ላይ በአባላትና ደጋፊዎች የሚገነቡ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈትቤት ሕንፃዎች ሥራ ለማስጀመር መሠረት ድንጋይ የማኖርና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም ማርሻሎ እንደገለጹት፤ በክልሉ ጠንካራ የአመለካከትና የሰው ኃይል አደረጃጀት ከመፍጠር ባለፈ ህዝብን በተሻለ ትጋት ማገልገል የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር ምቹ ሕንፃዎች መገንባት አስፈልጓል፡፡

በክልል ደረጃ እስከ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሊፈጁ የሚችሉ 48 ሕንፃዎች እንደሚገነቡ አቶ አብርሀም  አብራርተዋል ፡፡

የሕፃዎቹ ግንባታ እስከ አራት ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ዲዛይናቸውና ሥነ ውበታቸው ለከተሞች መልካም ገፅታ እንደሚፈጥሩና ለሌሎች ማስተማሪያ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።

ለህንፃዎቹ ግንባታ ከአባላቱና ከደጋፊዎች የሚያገኘውን ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡


 

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መኩሪያ ማርሻዬ በከተማዋ አራት ክፍለ ከተሞች ላይ የሚገነቡት ሕንፃዎች አጠቃላይ እስከ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጁ ጠቅሰዋል።  

ለእዚህም አባላትና ደጋፊዎቹ በገንዘብ፣ በዓይነትና በሙያ የተገኘ ድጋፍ የፓርቲውን አባላት ጥንካሬ እና በማንኛውም ተልዕኮ ላይ ያላቸውን ተነሳሽነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በገቢ ማሰባሰቢያው ላይ ድጋፍ ካደረጉ መካከል በግንባታ ማዕድን ቁፋሮና አቅራቢነት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ቦንጌ ዋኤ ለሕንፃ ግንባታው አሸዋና ጠጠር ከማቅረብ ባለፈ 1 ሚሊዮን 100 ሺህ ብር ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል ፡፡

"ከፓርቲውና ከመንግስት ጎን በመቆም አገራችንን ማልማት አለብን" ከሚል እሳቤ ተነስተው ድጋፉን ማድረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡

በሆቴልና በሕንፃ ሥራ ተቋራጭ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ጌቱ መታፈሪያ በሕንፃ ግንባታው አስፈላጊውን ሁሉ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

"በፓርቲው አመራር ሰጪነት በከተማችን የኮሪዳር ልማትን ጨምሮ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሰሩ ነው" ያሉት አቶ ጌቱ፤ "አቅሜ በፈቀደው ሁሉ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፍ እያደረግኩ ቀጥላለሁ" ብለዋል ፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ የፓርቲና የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም አባላትና ደጋፊዎች የተገኙ ሲሆን በጥሬ ገንዘብ 221 ሚሊዮን ብር ቃል ተገብቷል ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም