ቀጥታ፡

 በክልሉ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ይሰራል - ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ

ጋምቤላ፤ ጳጉሜን 5/ 2016  (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የተገኘውን ሰላም በአዲስ ዓመት በማጽናት ለህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

አዲሱ ዓመት ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን ርዕሰ መስተዳድሯ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሯ አዲሱን ዓመት አስመልክተው በላኩት መግለጫ የተገኘውን ሰላም በማጠናከር በአዲሱ ዓመት የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች በሚፈቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው ዓመት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሞ የቆየው የፀጥታ ችግር በህብረተሰቡና በፀጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት በአሁኑ ወቅት በክልሉ ሰላም በመስፈን ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ 

በመሆኑም በአዲሱ ዓመት ያለውን ሰላም ይበልጥ በማጠናከር በህዝቡ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሰጣቸው አብራረተዋል።

ቀደም ብሎ ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ በክልሉ ስኬታማ ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን ስኬታማ በማድረግ የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግም ሲባል ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ተደራሽ የማድረጉ ተግባር ሌላው የአዲሱ ዓመት ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሌላው በአዲሱ ዓመት ትኩረት ከሚሰጣቸው ዘርፎች መካከል የህዝቡን የንጹህ መጠጥ ውሃና የጤና አገልግሎትን የማሻሻል ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የሪፎርም ስራዎችን በማስቀጠል የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታቱ ሂደትም ሌላው ጉዳይ መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ መንግስት ለሚያከውናቸው ስራዎችና እቅዶች ስኬታማነት የክልሉ ህዝብ ድጋፍና ትብብር እንዲጠናከር ርዕሰ መስተዳድሯ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም