ቀጥታ፡

በአዲሱ ዓመት በግጭት ላይ የሚገኙ ወገኖች ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር ሊመጡ ይገባል - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ በአዲሱ ዓመት በግጭት ላይ የሚገኙ ወገኖች ሁሉንም ወገን አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር ሊመጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ጥሪ አቀረቡ።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሚሽኑ በ2016 ባወጣው መርኃ ግብር መሰረት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ከሚሽኑ አጀንዳ ለመሰብሰብ ተሳታፊዎችን ከወረዳ ጀምሮ በመለየት ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ያስመረጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከክልል ተሳታፊዎች ጋር በመሆን አጀንዳ እየሰበሰበ የመጣበት ጊዜ እንደነበር ጠቁመዋል።

በቀጣይም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ በሙሉ ልብ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገር ውስጥም በተለያዩ ምክንያቶች በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉንም አሸናፊና ተጠቃሚ ወደሚያደርገው ምክክር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲሱ ዓመት ሁሉንም ስሜቶቻችንን ወደ አመክንዮ በመቀየር ለሀገራችን የምንመክርበት ጊዜ ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

2017 ዓ.ም የሰላምና ከሁሉም በላይ የመተሳሰብ ጊዜ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም