የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ይዞ ተገንብቷል - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ይዞ ተገንብቷል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሜካናይዝድ ዕዝ ሀገርን ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ይዞ መገንባቱን የዕዙ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ከፍያለው አምዴ ገለጹ።
አዛዡ ይህን ያሉት የዕዙን ዝግጁነትና የአዲስ ዓመት ዋዜማን ምክንያት በማድረግ በዕዙ ማሰጠልኛ ማዕከል በተዘጋጀ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
ዕዙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ በሰው ኃይል፣ በሥነ-ልቦና እንዲሁም ዘመኑን በዋጁ ትጥቆች ራሱን በማደራጀት በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከተመሰረተ 74 ዓመታትን ያስቆጠረው የሜካናይዝድ ዕዝ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ታራካዊ ጠላቶች በየዘመኑ የሞከሯቸውን ሀገር የማፍረስ ዕኩይ ሴራዎች በማክሸፍ አኩሪ ገድል መፈፀሙን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሀገራችን ተፈጥሯዊ ኃብቷን ተጠቅማ እንዳትበለፅግና ሕዝቧ በሰላም እንዳይኖር እስከ ወረራ ሙከራ የደረሰ ሴራ ሲያሴሩ መኖራቸውን አስታውሰዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ጠላቶቿን በየጊዜው የሀፍረት ካባ በማልበስ የሚመልሱ ጀግኖችን የታደለች በመሆኗ፥ የጠላት ሙከራዎች በሙሉ ከሽፈዋል ብለዋል።
አሁንም የውስጥ ተላላኪ ባንዳዎችን በመጠቀምና በተሳሳተ ግምገማ ኢትዮጵያን ለመተንኮስ ቀቢጸ ተስፋ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል።
ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና መላው ሕዝቧ ከየትኛውም ኃይል የሚቃጣ ጥቃትን በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት የሀገር የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትን እንደሚያስከብሩም አረጋግጠዋል።
የሜካናይዝድ ዕዙም ሀገርን ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ በአንድ ጊዜ ብዙ ግዳጅ መፈፀም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ይዞ መገንባቱን ጠቁመዋል።
ወደፊትም የዕዙን ሁለንተናዊ አቅም የማሳደግና ሕዝባዊ ሰራዊት የመገንባት ሥራው ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።