ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለግብርና ናሙና ቆጠራ የሚውል የድጋፍ ሥምምነት ከፋኦ ጋር ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ለግብርና ናሙና ቆጠራ ስራ ድጋፍ የሚያገኝበት ሥምምነት ከዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጋር ዛሬ ተፈራርሟል።

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፋኦ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ ፈርመውታል።

በስምምነቱ አማካኝነት አገልግሎቱ 475 ሺህ ዶላር የገንዘብና የሙያ ድጋፍ ያገኛል።


 

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከርሻሌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ለዓለም አቀፍና ለአገር አቀፍ ለግብርና ፓሊሲ ግብዓት የሚሆን የግብርና ናሙና ቆጠራ በ2017 እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የቆጠራውን መረጃ የግብርናውን ትራንስፎሜሽንን ለማፋጠንና አዳዲስ የግብርና ሥልቶችን በመቀየስ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።።

ሥምምነቱ የባለሙያዎችን የቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅም የሚያሳድግ፣ ልምድና ተሞክሮ እንዲገኙ የሚያስችል በመሆኑ ባለሙያዎች ጥራት ያለውና ዓለም አቀፍ  ደረጃውን  የጠበቀ ቆጠራ እንዲያካሂዱ ያስችላል ነው ያሉት።


 

በኢትዮጵያ የፋኦ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ኢትዮጵያ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የምታካሂደው የግብርና ቆጠራ ለዓለም አቀፍና ለአገሪቱ የግብርና ፖሊሲዎች ግብዓት የሚውል መሆኑን አመልክተዋል።

ድጋፉ የግብርና ናሙና ቆጠራው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው እንዲሆን የሚያስችል ነውም ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም